Homeዜናና ወቅታዊዜናግብጽ በኔቶ አምሣል የዐረብ መከላከያ ኀይል እንዲቋቋም ያቀረበችው ዕቅድ በኳታር እና ኤምሬቶች...

ግብጽ በኔቶ አምሣል የዐረብ መከላከያ ኀይል እንዲቋቋም ያቀረበችው ዕቅድ በኳታር እና ኤምሬቶች ውድቅ ተደረገ

የግብጽ ባለሥልጣናት በሣምንቱ መጀመሪያ በኳታር ዶሐ በተከናወነው የሙስሊም እና ዐረብ ሀገሮች ጉባዔ ላይ ያቀረቡት በኔቶ አምሣል የሚቋቋም የዐረብ መከላከያ ኀይል ዕቅድ፤ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና ኳታር ውድቅ መደረጉን ሚድል ኢስት ዐይ የሀገሪቱን ዲፕሎማቶች ዋቤ በማድረግ ዘግቧል።

እንደ ዘገባው ከሆነ፣ የግብጽ ባለሥልጣናት ዕቅዱን ያቀረቡት አባል ሀገሮችን ከውጭ ሥጋት በተለይም ከእስራኤል ጥቃት ለመከላከል ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጥምረት ለመመሥረት እ.አ.አ በ1950 በተደረሰው የጋራ የመከላከያ እና የኢኮኖሚ ትብብር ውል መሠረት ነው።

ይሁን እንጂ በግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድር ዓልአጢ የቀረበው ዕቅድ በዋነኛነት በሁለቱ ሀገሮች ተቃውሞ ገጥሞታል። ለዕቅዱ ውድቅ መደረግ ዐቢይ ምክንያት ነው የተባለው ሀገሮቹ የመከላከያ ኀይሉ አዛዥነት ላይ ባለመስማማታቸው ነው። ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር ሳዑዲ ዐረቢያ አዛዥነቱን መውሰድ ትፈልጋለች። የግብጽ ሰዎች ደግሞ የረዥም ጊዜ ወታደራዊ ልምድ አካብተናል በማለት የተሻለ የአዛዥነት ሥልጣን ሊኖረን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።

በዕቅዱ ላይ የተደረገው ውይይት ያለ ፍሬ በተበተነ ማግሥት ሳዑዲ ዐረቢያ የኑክሌር መሣሪያ ከታጠቀችው ፓኪስታን ጋር የሁለትዮሽ የመከላከያ ስምምነት ተፈራርማለች። በአንፃሩ የግብጽ ፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አል ሲሲ ሐሳብን የባህረ ሰላጤው ሀገሮች ውድቅ በማድረጋቸው ዶሐን ለቀው የወጡት በ”ብስጭት” መሆኑን ዲፕሎማቶች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የዐረብና ሙስሊም ሀገሮችን የጋራ ግንባር ዕቅድ ለመስማት የተሰበሰበው ጉባዔ በአሜሪካ ተፅዕኖ ምክንያት ለጋዛ የድጋፍ መግለጫ በማውጣትና እስራኤልን በመኮነን ብቻ እንዲወሰን መደረጉን አንድ ዲፕሎማት ተናግረዋል። በዚህ ሒደት አስቀድመው ዋሺንግተን ተጉዘው የነበሩ የኳታር ልዑካን ይዘው የተመለሱት መልዕክት አስተዋፅኦ አድርጓል። ልዑካኑን የመሩት የዶሐ ባለሥልጣናት ለተሰብሳቢዎቹ የነገሯቸው በእስራኤል ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ማሳለፍ እንደሌለባቸው ነው።

የዐረብ ሙስሊም ሀገሮች አስቸኳይ ጉባዔ የተጠራው፤ እስራኤል በአሜሪካ በቀረበ የጋዛ ተኩስ አቁም ምክረ ሐሳብ ላይ በዶሐ እየመከሩ የነበሩ የሐማስ አመራሮች ላይ ጥቃት መሠንዘሯን ተከትሎ መሆኑ ይታወቃል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular