በፈረንሣይ ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረጉ “አድልዎ እና የዘረኝነት ስሜት” መስፋፋቱን የሚገልጽ አዲስ ጥናት ይፋ ተደርጓል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረት 82 በመቶ የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ሙስሊሞች ላይ ጥላቻ መንሰራፋቱን ገልጸዋል፡፡ ከምላሽ ሰጪዎች መካከል 81 በመቶ የሚሆኑት ጥላቻው የጨመረው ባለፈው ዐስር ዓመት ውስጥ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
የፈረንሣይ የሕዝብ አስተያየት ተቋም በሀገሪቱ የሚኖሩ አንድ ሺሕ ሙስሊሞችን ናሙና ወስዶ የሠራው ጥናት የታተመው፤ በቅርቡ የተቋቋመው በፈረንሣይ ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን መድልዎ በሚከታተል ተቋም ነው። ጥናቱ እንደሚያሳየው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ሁለት ሦስተኛ (66 በመቶ) የሚሆኑ ሙስሊሞች የዘረኝነት ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ቁጥር በአጠቃላይ ከፈረንሳይ ሕዝብ ላይ ከተመዘገበው 20 በመቶ እና በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ከተመዘገበው 18 በመቶ እጅግ የላቀ መሆኑን የሚድል ኢስት ዐይ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በጥናቱ መሠረት ዘረኛ ድርጊቶች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙት ሒጃብ በሚለብሱ ሴቶች ላይ ነው፡፡ ይህ 75 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከ25 ዓመት በታች ባሉ ወጣቶች 76 በመቶ፣ ጠንካራ የአነጋገር ቅላጼ ባላቸው ሙስሊሞች ላይ ደግሞ ከ81 በመቶ በላይ ተመዝግቧል፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ ተወላጆች ላይ ይህ አሐዝ 84 በመቶ ይደርሳል፡፡
በተጨማሪም በፈረንሣይ ከሚኖሩ ሦስት ሙስሊሞች መካከል ሁለቱ የሃይማኖት አድልዎ ሰለባ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህ ሁኔታ በአብዛኛው የሚከሰተው ሥራ በሚፈልጉበት ጊዜ (51 በመቶ)፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በሚውሉበት ጊዜ (51 በመቶ) እና መኖሪያ ቤት በሚፈልጉበት ጊዜ (46 በመቶ) ነው።
ገለልተኝነትን እንዲያንጸባርቁ በሚገደዱ የመንግሥት አገልግሎቶች ላይ ጭምር “ተለምዶአዊ መድልዎ” እንደሚስተዋል ይፋ ያደረገው ጥናት አድራጊው፤ በዚህም መሠረት 36 በመቶ የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች በሕዝብ አስተዳደሪዎች፣ የጤና ክብካቤ ባለሞያዎች እንዲሁም የትምህርት ቤት መምህራን አድልዎ ፈጽመውብናል ማለታቸውን ገልጿል፡፡ መድልኦው በጠንካራ የንግግር ቅላጼ መኖር፣ በአስቸጋሪ ሰፈሮች ውስጥ መኖር፣ ወጣት በመሆን እና ሒጃብ በመልበስ ሊባባስ ይችላል።
የዳሰሳ ጥናቱን በገንዘብ የሚደግፈው የፓሪስ ታላቁ መስጂድ አስተዳዳሪ ሸምሰዲን ሐፊዝ ውጤቱን ተከትሎ “ለተንሰራፋው ሙስሊም ጠልነት ምላሽ እንዲሰጥ” ጥሪ አቅርበዋል። “ሙስሊም ጠልነትን መዋጋት የሀገር ደኅንነት እና የሀገሪቱ አንድነት ጉዳይ ነው” ያሉት ሐፊዝ፤ “በዜጎቹ መካከል እንዲህ ያለው ልዩነት እንዲስፋፋ የሚፈቅድ ሀገር መሠረቱን ይንዳል” ሲሉ አስጠንቅቅዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሙስሊሞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ የጨመሩባት ፈረንሣይ፤ እስከ 6 ሚሊዮን የሚደርሱ ሙስሊሞች ይኖሩባታል ተብሎ ይገመታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












