Homeዜናና ወቅታዊዜናወንድ ልጃቸውን በእስራኤል የዶሐ ጥቃት የተነጠቁት ኸሊል አል ሐያ፣ አሜሪካ እና ጉቴሬዝ

ወንድ ልጃቸውን በእስራኤል የዶሐ ጥቃት የተነጠቁት ኸሊል አል ሐያ፣ አሜሪካ እና ጉቴሬዝ

የእስራኤል ጦር ማክሰኞ ከሰዓት በኳታር ዶሐ ለስብሰባ በተቀመጡ የሐማስ ከፍተኛ አመራሮች ላይ በሰነዘረው ጥቃት፤ የተደራዳሪ ቡድን መሪው ኸሊል አል ሐያ ወንድ ልጅ መገደሉን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል። በዘገባው መሠረት አባትዬው ኸሊል አል ሐያ፣ ከሌሎች የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ማለትም ኻሊድ መሻል እና ዛሒር ጀበሪን ጋር በሌላ ሥፍራ በስብሰባ ላይ ስለነበሩ ጥቃቱ ሳያገኛቸው ቀርቷል።

ከሐማስ አመራሩ ወንድ ልጅ በተጨማሪ የጽሕፈት ቤት ዳይሬክተሩ ጂሐድ ሉበድ እንዲሁም ሦስት ጠባቂዎች ተገድለዋል። ኸሊል አል ሐያ ከሌሎች አመራሮች ጋር ለስብሰባ የተቀመጡት በአሜሪካ በቀረበው የጋዛ ተኩስ አቁም ላይ ለመወያየት ነበር። በእስራኤል ጦር ዒላማ ተደርገው የተረፉት አል ሐያ መኖሪያቸውን ከጋዛ ውጪ ካደረጉ የሐማስ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ናቸው። ሰውዬው የቡድኑ የቀድሞ መሪዎች ኢስማኤል ሐኒያህ እና የህያ ሲንዋር ከተገደሉ በኋላ ይበልጥ ወደ ፊት ረድፍ መምጣታቸው ይነገራል።

አልጀዚራ እንደዘገበው፤ አል ሐያ በአሁኑ ሰዓት የፍልስጤሙን ቡድን ከሚመሩ አምስት ሰዎች መካከል ዋንኛው ሆነዋል። ከአል ሐያ ጋር ኢዘዲን አል ሐዳድ፣ ኻሊድ ማሻል፣ ሙሐመድ ደርዊሽ እና ኒዛር አዋደላህ ይገኙበታል። የ65 ዓመቱ ዕድሜ ያላቸው ኸሊል አል ሐያ፣ በርካታ ጊዜያትን የሚያሳልፉት ዶሐ ነው። በዶሐ መቀመጣቸው በአሜሪካ፣ ግብፅ እና ቡድኑን ባስጠለለችው ኳታር አማካይነት ለሚካሄደው የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር ከሀገር ሀገር በነፃነት እየተዘዋወሩ እንዲሠሩ አስችሏቸዋል ይባላል። አል ሐያ በትናንትናው እለት በዶሐ የጥቃት ዒላማ ከመደረጋቸው አስቀድሞ የእስራኤል መገናኛ ብዙኀን ከቀናት በፊት በተጓዙባት ቱርክ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል የሚል መረጃ አሠራጭተው ነበር።

ኸሊል አል ሐያ ወንድ ልጃቸውን በእስራኤል ጥቃት ሲነጠቁ የመጀመሪያው አይደለም። በ2014 የእስራኤል ወታደሮች ኦሳማ የተባለውን የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸውን መኖሪያ ቤት በቦምብ በማውደም ባለቤቱን ጨምሮ ከሦስት ልጆቹ ላይ ግድያ ፈጽሞበታል።

እስራኤል የሐማስ አመራሮችን ዒላማ በማድረግ የፈፀመችው ጥቃት ከአሜሪካ አስቀድሞ ይሁንታ ማግኘቱን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ይሁን እንጂ የኳታር ባለሥልጣናት ርምጃው እንደሚወሰድ ቀድሞ አልተነገረንም ብለዋል። ከጥቃቱ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኳታር አሚር ተሚም ቢን ሐማድ ደውለው ነበር።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ደግሞ ጥቃቱ የተፈፀመው በተዋጊ ጄቶች ነው። ጥቃቱን ከተፈፀመ በኋላ ዮርዳኖስ የአየር ክልል አለመፍቀዷን በመግለጽ በጥቃቱ እጃችን የለበትም ብላለች። ጥቃቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታች ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጎቴሬዝ አውግዘውታል። ጥቃቱ በአየር ክልሏ የተሰነዘረባት ኳታር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አስገብታለች። ምክር ቤቱም በአልጄሪያ እና ፓኪስታን ጥያቄ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ስብሰባው ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ዛሬ ረቡዕ ነው።

የእስራኤልን ጥቃት በማውገዝ ጣሊያን፣ ስዊዘርላንድ፣ ፖርቹጋል እና ቤልጂየም መግለጫ አውጥተዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular