መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው በድር ኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ የዲያስፖራ ወኪሎች ምርጫ ሒደት ውጤት “ለማንም ጥቅም የማይሰጥ፣ ጊዜና ሐብትን ያባከነ [ነው]” ሲል ነቀፌታ ሰንዝሯል። ድርጅቱ በሰሜን አሜሪካ የዲያስፖራ ተወካይ በመባል የተመረጡት ግለሰብ ምርጫም “በዘፈቀደ የተደረገ” ነው ሲል አሳውቋል።
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ 27 ኮሚኒቲዎችን በስሩ ማቀፉን የሚገልፀው በድር ኢትዮጵያ፤ በቦርዱ ምርጫ ሒደት ላይ ተቃውሞን የገለጸው ጳጉሜን 3/2017 ባወጣው መግለጫ ነው። የድርጅቱ መግለጫ የመጣው ጳጉሜን 2/2017 በተጠናቀቀው የ2017 ምርጫ፣ አስፈጻሚ ቦርዱ አምስት የዲያስፖራ ተወካዮች መመረጣቸውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው። ቦርዱ ከአሜሪካ ተመርጠዋል ያላቸው ግለሰቦች ፉዓድ ዓብዱልከሪም እና ሸይኽ ዓሊ ሙሐመድ ናቸው።
ይህን እንጂ በድር ኢትዮጵያ በምርጫው ሒደት በድርጅቲም ሆነ በስሩ የታቀፉ ኮሚኒቲዎች መርጠው የላኩት ተወካይ አለመኖሩን በመግለጽ፣ ውይይትና ምርጫ ባላደረጉበት ሁኔታ ወኪል መሾሙ “ፍፁም አግባብ ያልሆነና ወደፊት ዲያስፖራው ከመጅሊሱ ጋር በጋራና በትብብር የሚሠራበትን መንገድ ከወዲሁ በእንቅፋት ለማጠር የተጠነሰሰ ሙከራ ነው” ብሎታል።
አክሎም ተፈጽሟል ያለው ድርጊት “እንዳይከናወን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢውን ጨምሮ በተለያየ ጊዜ የመጅሊሱን አመራሮች ያነጋገረ ቢሆንም በቅድሚያ የታቀደ በሚመሰል መንገድ” እስላማዊ አሠራርንም ሆነ የምርጫ ህግን በጣሰ መልኩ የዲያሰፖራ ወኪሎች በማለት “ከተቋማት ጋር ሳይሆን ከግለሰቦች ጋር መጓዝን” መመረጡንም ገልጿል።
የሰሜን አሜሪካን የዳያስፖራ ውክልናን በሚመለከት ወደፊት የውክልናውን ዝርዝር ኀላፊነትና ሚና ከመጅሊሱ ጋር አስፈላጊው ዉይይት ተደርጎ “ሁሉን ባሳተፈና ግልጽ በሆነ መንገድ መርጦ መላክ እንደሚቻል”ም አሳውቋል።
መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው በድር ኢትዮጵያ፤ በመጅሊስ ሀገራዊ ምርጫ ሂደትም ሆነ የዲያስፖራ ምክር ቤትን ለመመሥረት መጅሊሱ እንቅሰቃሴ ሲያደርግ “ካለን ቅርበት አኳያ እንደማንኛውም ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ ማወቃችን እንግዳ ነገር ነው” በማለት ሒደቱን በመቃወም የልዑካን ቡድን በመላክና በደብዳቤ ጥያቄውን ለመጅሊሱ ፕሬዝዳንት በከፍተኛ አመራሮች በአካል ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ የገለጸው ከሁለት ሣምንት በፊት ነበር። ድርጅቱ በወቅቱ ላቀረበው ቅሬታ በቦርዱ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።
ቦርዱ እሑድ እለት ባከናወነው ምርጫ፣ ከአሜሪካ በተጨማሪ ሙሐመድ ሙስጠፋ ከእንግሊዝ፣ ዓብዱረህማን ሑሴን ከናይሮቢ እና ዓብዱ ሰዒድ ከሪያድ የዲያስፖራ ተወካይ ተደርገው መመረጣቸውን ይፋ አድርጓል። (ሚንበር ቲቪ)












