የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ የፍልስጤማውያን ቪዛ አመልካቾችን ጥያቄ መቀበል ማቆሙን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ከፍልስጤም አስተዳደር የሚሰጠውን ፓስፖርት ውድቅ የሚያደርገው አዲሱ መመርያ፤ ባለፈው ወር አጋማሽ ለሁሉም የአሜሪካ ኤምባሲዎች ተላልፏል፡፡
ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ርምጃው የተወሰደው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በጋዛ የቆሰሉ ፍልስጤማውያን ሕፃናት ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ በአክራሪ ቀኝ ዘመም አክቲቪስቱ ላውራ ሉመር ጫና ከተደረገበት በኋላ ነው። በትራምፕ አስተዳደር ስር ተፅዕኖ አሳዳሪ ድምፅ ሆኖ የወጣው ሉመር፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕፃናት “የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት” ናቸው ሲል የፈረጀ ነው፡፡ ዘገባው አክሎም የፍልስጤም ፓስፖርት በያዙ ላይ የተጣለው ክልከላ የፍልስጤምን ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ለማዳፈን የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በእገዳው መሠረት የንግድ ጉዞን ጨምሮ ከፍልስጤማውያን የሚቀርብ ማንኛውንም ዐይነት የአሜሪካ ቪዛ ጥያቄ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች ሀገሮችን ፓስፖርት የያዙ ፍልስጤማውያን እንዲሁም ቀድሞ ቪዛ ያገኙትን ክልከላው አይመለከትም፡፡
አሜሪካ በተመሳሳይ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ እና 80 ባለሥልጣናትን ቪዛ በመሰረዝ በሚቀጥለው ወር በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳይገኙ ከልክላለች፡፡ አሜሪካ የባለስልጣናቱን ቪዛ የሰረዘችው ፈረንሣይና ካናዳን ጨምሮ አንዳንድ ሀገሮች ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና እንሰጣለን ማለታቸውን ተከትሎ ነው። በዚህ ጉባኤ ላይ የአሜሪካ አጋር ዩናይትድ ኪንግደም በእስራኤል ላይ ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ ዕውቅና እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ ለቪዛ ክልከላው በፍልስጤም አስተዳደር ድጋፍ የሚሰጠውን በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት እና ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ የቀረበውን የጦር ወንጀል እና የዘር ፍጅት በምክንያት ጠቅሳለች፡፡
በአሜሪካ ለዜጎች በሚሰጠው ፓስፖርት ላይ ክልከላ የተጣለበት የፍልስጤም አስተዳደር የበላይ ተቆጣጣሪ የፍልስጤሙ ፈትሕ ነው፡፡ የፍልስጤም ፓስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ መስጠት የተጀመረው አሁን በፍልስጤም አስተዳደር የሚወከለው የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) እ.አ.አ በ1990ዎቹ ትጥቅ በመፍታት ከፊል ጋዛ እና ዌስት ባንክን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት አሁን በፍልስጤም አስተዳደር ላይ ክልከላ ቢጥልም በታሪክ ለአስተዳደሩ በሚሰጠው ድጋፍ ይታወቅ ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












