የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፤ እንደ ሐጅ እና ኡምራ ዐይነት ሃይማኖታዊ ጉዞዎች በሚካሄዱበት ወቅት በረራሮችን ከክልሎች ቀጥታ ለማድረግ የመንግሥት አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ዕቅዱ በሒደት ላይ እንደሚገኝ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ይህን የገለጸው በ2018 የክልል አየር ማረፊያዎችን አቅም በማጎልበት መንገደኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እንደሚደርግ በገለጸበት ወቅት ነው፡፡ በባለሥልጣኑ መረጃ መሠረት፤ በተለይ እንደ ሐጅና ዑምራ ዐይነት ሃይማኖታዊ ጉዞዎች በሚካሄዱበት ወቅት የክልል አየር ማረፊያዎች በተለይ ከባሌ ሮቤ፣ ከጅግጅጋ፣ ከአሶሳ፣ ከሰመራ እና ድሬዳዋ ከተሞች በርካታ ተጓዦችን ወደ አዲስ አበባ በማሳፈር፤ ከመዲናዋ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚያደርጉት ጉዞ “አላስፈላጊ መጉላላትን የሚያደርስ ብቻ ሳይሆን በአየር መንገዱ ላይ አላስፈላጊ ጫና” የሚፈጥር ነው፡፡

በመሆኑም ጉዞውን በማሳጠር ተጓዦች “ካሉበት ክልል በቀጥታ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ጉዞ ማድረግ የሚችሉበት መንገድ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን” ያስታወቀው ባለሥልጣኑ፤ “የመንግሥትም አቅጣጫ ጭምር በመሆኑ” ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ ከጉምሩክ፣ ከኢምግሬሽንና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ጋር “በመነጋገርና መግባባት ላይ በመድረስ” ጉዳዩ እልባት እንደሚያገኝ መሥሪያ ቤቱ ያለውን እምነት ገልጿል።
የበረራውን ዕቅድ በተመለከተ ለ“ሚንበር ቲቪ” የተናገሩት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዐብዱልፈታህ ሙሐመድ፤ የምክር ቤቱ ኃላፊዎች ስለ ጉዳዩ መረጃ እንዳላቸው አረጋግጠዋል፡፡ ዕቅዱ በቀዳሚነት የተነሳው በ2016 ተግባራዊ በተደረገው ሁሉም የክልል ተመዝጋቢ ምዕመናን በመኖሪያ አቅራቢያ በተከፈቱ ጣቢያዎች እንዲስተናገዱ በተደረገበት ወቅት እንደነበር በማስታወስ፤ በተለይ በሐጅ ወቅት በርካታ የቁጥር ድርሻ ያላቸውን የጅግጅጋ እና ጎዴ ተመዝጋቢዎች ለማስተናገድ እንደ እቅድ ቀርቦ ነበር ብለዋል፡፡ ዕቅዱን አሁንም ተግባራዊ ለማድረግ በሒደት ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ሲጠናቀቅ ሊጀመር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
እንደ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከሆነ፤ በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በተጨማሪ የባሕር ዳር፣ የመቀሌ፣ የድሬዳዋ አየር ማረፊያዎች ዓለም አቀፍ ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












