Homeዜናና ወቅታዊዜናበዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ያመርታል ለተባለ የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ...

በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ያመርታል ለተባለ የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት የተፈራረመው ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 22/2017 ነው፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዐቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምምነቱን በተመለከተ በይፋዋ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባሠፈሩት ጽሑፍ፤ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ይፈስበታል ያሉት ሜጋ ፕሮጀክት፤ በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እንደሚያመርት ገልጸዋል፡፡ ይህ የምርት መጠን “ኢትዮጵያን ከአለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ ያደርጋታል” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ፕሮጀክቱ በሀገር ውስጥ የሥራ እድል እንደሚፈጥር፣ ለዘመናት ለተፈተኑት ገበሬዎች አስተማማኝ የማዳበሪያ አቅርቦት እንደሚያረጋግጥ እና መንግሥት “ለምግብ ሉዓላዊነት ወሳኝ ርምጃ መውሰዱን” አመላካች እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

የዛሬውን የፊርማ ስምምነት ተከትሎ ፋብሪካው በሚቆምበት ሥፍራ ፕሮጀክቱ በይፋ እንደሚጀመር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን” ሲሉ አስፍረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ እንደምታስጀምር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገሩት ሰኔ 26/2017 በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ ሥራ የሚጀምረው “ከ40 ወራት በኋላ” እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular