Homeዜናና ወቅታዊዜና“ጋዜጠኞቻችን የግድያ ዒላማ ውስጥ የገቡት በሞያቸው ምክንያት ነው” - የሚድል ኢስት ዐይ...

“ጋዜጠኞቻችን የግድያ ዒላማ ውስጥ የገቡት በሞያቸው ምክንያት ነው” – የሚድል ኢስት ዐይ ዋና አዘጋጅ ዴቪድ ኸርስት

ዋና መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ሚድል ኢስት ዐይ፤ ሙሐመድ ሰላማ እና አሕመድ አቡ አዚዝ የተባሉ ባልደረቦቹ በእስራኤል ወታደሮች የተገደሉት በሞያቸው ምክንያት ተለይተው መሆኑን ዋና አዘጋጁ ዴቪድ ኸርስት ገልጿል፡፡

ዋና አዘጋጁ ይህን የገለጸው ለብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ የዋና አዘጋጁ ደብዳቤ የተጻፈው ጋዜጠኞቹ በኻን ዩኒስ ከሌሎች ባልንጀሮቻቸው ጋር መገደላቸው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ቁጣ ከቀሰቀሰ በኋላ ነው፡፡ በጥቃቱ የአስሸየትድ ፕረስ እና ኢንዲፔንደንት ዐረቢያ ፍሪላንሰር ፎቶ ጋዜጠኛዋ መርየም አቡ ደቃ፣ ለሬውተርስ የሚሠራው ሑሳም አል ሚስሪ እና ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በፍሪላንስ የሚዘግበው ሙዓዝ አቡ ጠሃ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል፡፡

ኸርትስ ትናንት ረቡዕ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ፤ ሁለቱ የሚድል ኢስት ዐይ ባልደረቦች በእስራኤል ባለሥልጣናት ዒላማ ውስጥ ያስገቧቸውን ዘገባዎች እንዲሁም በየትኛው የእስራኤል ባለሥልጣን ማንነታቸውን ጨምሮ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች እንደተለየ መረጃ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ የተፈጸመውን ጥቃት ዝርዝር ማጋለጥ ሌሎች በሕይወት የተረፉ ጋዜጠኞችን አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል ይፋ ከማድረግ ተቆጥበናል ብሏል፡፡

ዴቪድ ኸርስት በዋና አዘጋጅነት የሚመራው ሚድል ኢስት ዐይ፤ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን አፍሪካ እና ሰፊው የሙስሊሙ ዓለም ሀገሮች ላይ በማተኮር ዜና፣ ፊቸር እና አስተያየት የሚያሠራጭ ድረ ገጽ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2011 የተመሠረተው ሚድል ኢስት ዐይ፤ በኳታር መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለታል ቢባልም ድረ ገጹ ግን በይፋ ያስተባብላል፡፡ ክሱ የሚቀርበው በሳዑዲ ዐረቢያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ ግብጽ እና ባሕሬን ነው፡፡

ከእነዚህ ሀገሮች መካከል የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በ2016 የሚድል ኢስት ዐይ ድረ ገጽ በሀገሯ እንዳይታይ አግዳ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የፕሬዝዳንት ዐብዱልፈታህ አል ሲሲ አስተዳደር በ2019 በግብጽ ምድር ድረ ገጹን እንዳይታይ ያገደ ሲሆን፣ ዮርዳኖስ ደግሞ ተመሳሳይ ርምጃ የወሰደችው በግንቦት 2025 ነበር፡፡ የዮርዳኖስ እግድ የመጣው ሀገሪቱ ወደ ፍልስጤም መሬት ጋዛ ርዳታ ለማስገባት ከፍተኛ በጀት የሚመድቡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ማገዷን የሚያጋልጥ ዜና ካሠራጨ በኋላ ነው፡፡

የሚድል ኢስት ዐይ ድረ በ2020 በመንታፊዎች የጥቃት ኢላማ ከተደረጉ 20 ዓለም አቀፍ ድረ ገጾች መካከል እንደነበር የሣይበር ደኅንነት ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular