በረቢዕ፡

ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ቁርኝት ባለው በረቢዕ አል-አወል ወር አራተኛ ቀን ላይ ተገኝተናል፡፡ በወሩ የዓለም ብርሃን ከሆኑት ከመልዕክተኛው ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን በ“ሚንበር ቲቪ” ሁሉም መዳረሻዎች እያነሳሳን እንቀጥላለን፡፡ በቴሌቪዥን፣ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና በሁሉም፡፡

ዛሬ ታላቁን ነቢይ ወዳበቀለችው ሳዑዲ ዐረቢያ መካ ከተማ ተጉዘናል፡፡ በዚያ ትናንት ማክሰኞ በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሕይወት በኢስላም ሥልጣኔ ላይ የሚያተኩር አውደ ርዕይ ተከፍቷል፡፡ በአውደ ርዕዩ የነቢዩ ሙሐመድን ሕይወት ከኢስላም ሥልጣኔ ጋር በማጣመር ዘመን በደረሰበት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለጎብኚዎች ቀርቧል፡፡ አዘጋጆቹ ጉብኚዎቻችን ሲመጡ መልዕክተኛው “አብረዋቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው እናደርጋለን” የሚል ውጥን መያዛቸውን ዐረብ ኒውስ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡  

በተዘጋጀው ዲጂታል አማራጭ ጉብኚዎች ከመልዕክተኛው ጋር በመካ፣ በመዲና እና በስደት ዘመናቸው እንዲሁም በሌሎችም የሕይወት መንገዶች እንዴት እንዳለፉ ይመለከታሉ፡፡ ነቢያዊ ሕክምናዎችን መማር እና የዕለት ተእለት ኑሯቸውን መቃኘትም የአውደ ርዕዩ አካል ነው፡፡ አዘጋጁ ሙስሊም ወርልድ ሊግ እና ከመካ ከተማ እና ቅዱስ ሥፍራዎች አስተዳዳሪ አካል ጋር በትብብር እንዳዘጋጀው ተገልጿል፡፡

መካ ከደረስን ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከተማ መዲና መሻገር ይኖርብናል፡፡ ከመልዕክተኛው ጋር በምትነሳው ከተማ ስር፤ የሀገሩ ባለሥልጣናት ሁሉም ነገር ስለ እርሳቸው በሚጣራው ከተማ አንድ ምዕመን የመልዕክተኛውን ሕይወት ሁሉንም ጉዳይ በአንድ ሥፍራ ማግኘት ከፈለገ ሳይጎበኘው መሄድ የለበትም የሚሉትን ሙዝየም እናገኛለን፡፡ ከመስጂድ አን ነበዊ ጎን የሚገኘው ሙዝየሙ ዓመቱን ሙሉ ለ24 ሰዓት ክፍት የሚደረግ ነው፡፡ ስለ ሙዝየሙ የተጻፉ መረጃዎች ጉብኚዎች ወደ ውስጥ ሲዘልቁ በዓለማችን ሰባት ቋንቋዎች ማብራሪያ ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጹ ናቸው፡፡ ዐረቢኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ስፓኒሽ፣ ኡርዱ፣ ፈረንሳይኛ፣ ቱርክኛ እና የኢንዶኔዥያ ቋንቋም በዝርዝሩ አልቀረም፡፡ በርግጥ የእኛን ሀገር ቋንቋ አናገኝም፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ የሚጓዙ ጉብኚዎች በቋንቋ ሊቸገሩ ስለሚችሉ አማራጭ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ስለ ነቢዩ ሕይወት ተከታታይ ፊልሞችን ማሳያ በውስጡ ተካቷል፡፡ መዝየሙ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ሴቶች የነበራቸውን ጉልሕ ሥፍራ ለማሳየት፤ ከእዝነቱ ነቢይ አጠገብ ቁልፍ ሚና የነበራቸውን እንስቶች ይዘክራል፡፡

መልዕክተኛው ሕፃናትን በእንዴት ያለ መልኩ ይንከባከቡ ነበር ለሚሉም ምላሽ አለው፡፡ ይህ ወላጆች በዚያው ልጆችን እንዴት ማሳደግ እንደሚኖርባቸው ትምህርት እንዲቀስሙ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ በሙዝየሙ የነቢዩ ሙሐመድን ዘመን በምልሰት ለማምጣት ሁሉም ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋሉን ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ የተወዳጁን ነቢይ መልክ እና ባሕርይ ለመግለጥም (ለማብራራት) ሙከራ አድርጓል፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ የመልዕክተኛውን መጫሚያ፣ የቤት ቁሳቁስ እና አልባሳት ሁሉ አልቀሩትም፡፡ ሙዝሙን የገነቡ አካላት እንዲያው ቢሆንልን በመላው ዓለም ይህን መሣይ ሙዝየም የመክፈት እቅድ አለን ማለታቸውም ተጽፎ ይገኛል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular