Homeዜናና ወቅታዊዜና“ረሒቀል መኽቱም”ን ለረቢዕ ወር እንደ ማጣፈጫ

“ረሒቀል መኽቱም”ን ለረቢዕ ወር እንደ ማጣፈጫ

በሂጅሪ ዘመን ቀመር ሦስተኛው ወር ረቢዕ አል-አወል ዛሬ ሦስተኛው ቀን ላይ ደርሷል፡፡ ከታላቁ ነቢይ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በሚቆራኘው ወር፤ የመልዕክተኛውን ሕይወት በጥልቀት ለማወቅ ከሚያግዙ መጻሕፍት መካከል “ረሒቀል መኽቱም” ከፊት ረድፍ የሚቀመጥ ነው፡፡

መጽሐፉ በቀዳሚነት የታተመው በዐረቢኛ ቋንቋ ሲሆን፣ አዘጋጁ ደግሞ ሕንዳዊው ሸይኽ ሶፊዩራሕማን አልሙባረ ከፉሪ ናቸው፡፡ ለአንባቢያን ከቀረበ 45 ዓመት ያስቆጠረው ይህ መጽሐፍ፤ መቀመጫውን ሳዑዲ ዐረቢያ መካ ከተማ ያደረገው የዓለም ሙስሊሞች ሊግ በፓኪስታን ባደረገው ጉባኤ በነቢዩ ሙሐመድ ታሪክ (ሲራ) ላይ የሚጻፉ ጥናቶችን አወዳድሮ እንደሚሸልም ማሳወቁን ተከትሎ በተለያዩ ቋንቋዎች ከተዘጋጁ ከ171 ሥራዎች መካከል ተወዳዳድሮ በአንደኛነት የተመረጠ ነው፡፡ በወቅቱ ለጸሐፊው 50 ሺሕ ሪያል ያስገኘው መጽሐፍ፤ ለአራት ዐስርት ዓመታት በመላው ዓለም በተለያዩ ቋንቋዎች በሙስሊሞች ቤት ለልጅ አዋቂው የመልዕክተኛውን ታሪክ ማስተማሪያ መሆኑ ሆኖ ያገለግላል፡፡

መጽሐፉ በእንግሊዝኛ “The Sealed nectar” በሚል ርእስ ይታወቃል፡፡ በዑርዱ፣ ቤንጋሊና ሌሎችም ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡ በኢትዮጵያም ዕውቁ የመጻሕፍት አዘጋጅ ኡስታዝ ሐሰን ታጁ ከ15 ዓመት በፊት ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰውታል፡፡ ተርጓሚው ወደ አማርኛ ሲመልሱት ርእሱን ሳይነኩት የዐረቢኛውን “ረሒቀል መኽቱም” ባለበት ማቆየት መርጠዋል፡፡

ወደ መጽሐፉ ይዘት ስንመጣ፤ ከዐረቦች ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና የዘር ግንድ በመጀመር፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ታሪክ፣ የቅድመ ኢስላም ዐረባዊ ማኅበረሰብ ዐበይት ገጽታዎች፣ የነቢዩ ሙሐመድ የዘር ሐረግ እና ቤተሰብ፣ ከልደት እስከ ነቢይነት ያለው ሒደት፣ ወደ አላህ ጥሪ የማድረግ ትግል የተካተተበት የመጀመሪያው እርከን ተብሎ የሚጠቀሰው መካዊ የነቢይነት ዘመን፣ ወደ እስልምና ይፋዊ ጥሪ ያደረጉበት ዘመን፣ ሦስተኛውና ከመካ ውጪ ወደ ኢስላም የተደረገው ጥሪ፣ የኢስራእ ጉዞና እርገት፣ የመጀመሪያውና ሁለተኛ የአቀባህ ቃል ኪዳን፣ የስደት ሕይወት፣ ሕይወት በመዲና፣ ከአይሁዶች ጋር የተደረገው ስምምነት፣ የትጥቅ ትግል፣ በኢስላም ታሪክ የመጀመሪያው ወሳኝ ጦርነት ነው የሚባለው ታላቁ የበድር ዘመቻ፣ በበድር እና ኡሁድ ዘመቻዎች መካከል ያለው ጊዜ፣ የኡሁድ ዘመቻ፣ የአህዛብ ዘመቻ፣ የበኒ ሙስጠለቅ ዘመቻ፣ ጉዞ ወደ መካ፣ ከንጉሣን እና ልዑላን ጋር ያደረጓቸው የመልዕክት ልውውጦች፣ መካን የማቅናት ዘመቻ፣ የሁነይን ዘመቻ፣ ከፈትህ ዘመቻ በኋላ የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶች እንዲሁም ነቢያዊ ጎጇቸው ምን መሣይ ነበር የሚለው በዝርዝር የተቃኘበት የተቃኘበት ነው፡፡

ክቡራን ተከታታዮች “ረሒቀል መኽቱም”ን ተቀምጠን እንከታተል የምትሉ ከሆነ፤ “በሚንበር ቲቪ” ዘወትር ሐሙስ በሚቀርበው “ሚንበሩል ዒልም” በኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እንዲከታተሉ ጥቆማ በማቅረብ፤ በረቢዕ ወር የ“ረሒቀል መኽቱም”ን ገጾች እየገለጥን ከመልዕክተኛው ጣፋጭ ሕይወት ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular