የአሜሪካ መንግሥት ሊቢያ ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን የምትቀበል ከሆነ፤ ለበርካታ ዓመታት ታግዶ የቆየው በቀድሞ መሪዋ ሙዓመር ቀዛፊ እና ቤተሰቦቻቸው ሥም የተመዘገበውን ንብረት እንደምትለቅ ሚድል ኢስት ዐይ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘውና መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው የሀገሪቱ መንግሥት፤ ከእስራኤል ጋር በጋዛ ጉዳይ ይፋዊ ድርድር እያካሄደ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ድርድሩን የሚያካሄዱት “ሑኩማት አል ዋህዳ አል ወጠኒያ” በመባል የሚጠራው የመንግሥት አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብዱልሐሚድ ደበይበህ የቅርብ ዘመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ኢብራሂም ደበይባህ ናቸው፡፡ ድርድሩን የሊቢያ፣ ዐረብ እና የአውሮፓ ሀገሮች ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል፡፡ ሥማቸው ያልተጠቀሰ የሊቢያ ባለሥልጣን፤ ንግግሩ መጀመሩን ቢያረጋግጡም ዝርዝር ጉዳዮችን ግን አስተባብለዋል፡፡
የሊቢያ ተጨማሪ ምንጭ ውይይቶቹ አሁንም በሒደት ላይ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በተለይ በፓርላማ አባላት ዘንድ ከፍተኛ የፍልስጤም ደጋፊነት ስሜት በመኖሩ ተደራዳሪዎች መረጃው ይፋ እንዳይደረግ ሠርተዋል፡፡ የሊቢያ መሪዎችን ለማረጋጋት ሲባል አሜሪካ ሀገሪቱን በኢኮኖሚ ረገድ ለመደገፍ እና ጥቅማ ጥቅሞችን ለመስጠት ዝግጁ ሆናለች፡፡ አሜሪካ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብዱልሐሚድ ደበይበህ ለሚመራው አስተዳደር በቀድሞው መሪ ሙዓመር ቀዛፊ ንብረትነት የተመዘገበውን 30 ቢሊዮን ዶላር ለመልቀቅ ቃል የገባችውም በዚሁ መነሻ ነው፡፡ ይለቀቃል የተባለው ንብረት ከ14 ዓመት በፊት በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ወቅት የታገደ ነው፡፡

ሊቢያ ከጋዛ ለሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያን መኖሪያ ልትሆን ትችላለች የሚለው ዜና የተሠራጨው፤ የሊቢያው ወታደራዊ መሪ ኸሊፋ ሐፍታር በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ለመቀበል ከተስማማ “በሀገሪቱ የነዳጅ ሐብት ላይ የበለጠ ቁጥጥር የሚያስገኝለት” ምክረ ሐሳብ ቀርቦለታል የሚሉ መረጃዎች ከወጡ በኋላ መሆኑም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ በሊቢያ በደረሰው አስከፊ ጥፋት እና አለመረጋጋት እንዲሁም በአጎራባች ሱዳን በተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል የሚባለው ሐፍታር ሪፖርቶችን አስተባብሏል።

እንደ ሐፍታር ሁሉ ሚድል ኢስት ዐይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብዱልሐሚድ ደቢይበህ ከሁለት ቀን በፊት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቤላቸው መስማማታቸውን ከገለጹ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፤ መንግሥታቸው “ፍልስጤማውያን እንዲሰደዱ በማድረግ ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንደማይኖረው” ተናግረዋል ብሏል፡፡
እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማባረር አጀንዳ በይፋ እያራመደች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ከበርካታ ሀገሮች ጋር ግንኙነት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን በማፈናቀል ወደ ሌሎች ሀገሮች እንዲሰደዱ የማድረግ ዕቅድ በይፋ የተዘገበው ከአንድ ወር በፊት ነው፡፡ በወቅቱ ሞሳድ በመባል የሚጠራው የእስራኤል የስለላ ድርጅት ዳይሬክተር ዴቪድ ባርኔያ፣ ዋሽንግተን ደርሰው ከትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በዘገባዎች መሠረት የስለላ ኀላፊው ከዋይት ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑኩ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ እስራኤል ከሊቢያ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ ጋር ነዋሪዎቹን ለማስፈር ንግግር ጀምራለች፡፡ የዘገባውን መውጣት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው ምላሽ የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












