የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ፤ በምርጫው ሒደት የሚነሱ ቅሬታዎችን መቀበል መጀመሩን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሰዒዳ ኸድር፤ ከሌሎች ኮሚቴ አባላት ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ በምርጫው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመስማት ከመስጂድ እስከ ፌዴራል ደረጃ ቅሬታ ሰሚ መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ማንኛውም ቅሬታ ያለው አካል በምርጫው የሚያነሳውን ቅሬታ በየደረጃው ባለው የቅሬታ ሰሚ ማቅረብ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ የቅሬታ አቀራረቡን ሒደት በተመለከተም በቀዳሚ እርከን የቀረበ ቅሬታ በተከታዩ ደረጃ የሚያገኘው ምላሽ የመጨረሻ ይሆናል ብለዋል፡፡
በፌደራል ደረጃ የተቋቋመው ቅሬታ ሰሚ በክልል ምላሽ ተሰጥቷቸው በድጋሚ እንዲታዩ አቤቱታ የሚቀርብባቸው ጉዳዮች እንደሚመለከት ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ ባዘጋጀው የአጭር ስልክ ቁጥር ቅሬታ ማቅረብ ይቻላል ተብሏል፡፡
ወይዘሮ ሰዒዳ ኸድር በሰብሳቢነት የሚመሩት የፌዴራል ምርጫ ቦርድ ቅሬታ ሰሚ፤ ሐጂ ሰዒድ ያሲንን በምክትል ሰብሳቢነት፣ አቶ ዓብዱልሐኪም ጀማልን በጸሐፊነት እንዲሁም ሐጂቢያ አባ መጫ አባ ሲመል፣ ሐጂ አሎ ሑሴን እና ሐጂ አደም ቢዳሪን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












