ለግብጻውያን እ.አ.አ ሐምሌ 14/2013 ትውስታው በመልካም የሚያነሱት አይደለም፡፡ በዚህ ቀን በሀገሪቱ በዴሞክራዊ ምርጫ ያሸነፉት ሙሐመድ ሙርሲ ለአንድ ዓመት ከጥቂት ቀናት የቆየው የፕሬዝዳንትነት መንበራቸው የተደፈረበት ነው፡፡
በእለቱ ሙርሲ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተደረገ፡፡ በወቅቱ ነገሩ ሁሉ የሆነው በአስደንጋጭ ፍጥነት ነበር፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ተዋናይ ደግሞ በፕሬዝዳንት ሙርሲ የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ተደርገው የተሾሙት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ወታደሩ ዓብዱልፈታህ አልሲሲ ናቸው፡፡
በአሜሪካ ፔኒስልቪንያ የጦር ኮሌጅ የወታደራዊ ሣይንስ ያጠኑት አል ሲሲ፤ ለአፍታ በርቶ በጠፋው የሙርሲ ሥልጣን ዘመን፤ በተለይ በመጨረሻ ወራት ሲያልጎመግሙ እንደነበር የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች በርካታ ናቸው፡፡ ከግብጽ አጋር አሜሪካ ሠራዊት ጋር ወዳጅ የሆኑት ሰው፤ የሙርሲን ሥልጣን የፈነቀሉት “ምንም እንኳ ጦራችን በእንደዚህ ዐይነት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ባይችልም ሕዝብን ቅር ስላሰኙ” በሚል ነው፡፡ በሕዝብ ያመካኙት የቀድሞ ወታደር “ሀገራችንን ለማዳን እንገደዳለን” ብለው በአደባባይ ለማወጅ አላመነቱም፡፡
የሙርሲ ሥልጣን ከተፈነቀለ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው የቁም እስር ላይ እንዲቆዩ ተደረገ፡፡ ጥቂት ቆይተው ደግሞ ወሕኒ ቤት ተወረወሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት ሙርሲን በእልልታ ለተቀበሏቸው ደጋፊዎቻቸውና ለግብፃዊያን ዴሞክራሲ ናፋቂዎች የሆነው ሁሉ የሚዋጥ አልነበረም፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ከአንድ ዓመት በፊት ደስታ ያስተናገዱ ጎዳናዎች በተቃውሞ ተሞሉ፡፡
አንዱ ከሌላው ጋር እየተጠራራ የራቢዓ እና የአል ናህዳ አደባባዮችን ሰው ሞላቸው፡፡ ቀን – ቀናትን እየወለደ ሳምንት ሞላ፡፡ ሳምንቱ በሌላ ሳምንት እየተተካ ለወር በጎዳና ውሎ ማደር፤ እዚያው መብላትና መጠጣት እና ለሰላት መቆም የሙርሲ ደጋፊዎች ሥራ ሆነና ከወታደሮች ጋር ፍጥጫው እየተካረረ የራቢዓ እና አልናህዳን ጎዳናዎች የሞሉት ግብጻዊያን ቁጥር 85 ሺሕ ሲደርስ ግብጻውያኑን አሁን ድረስ ሐዘን ውስጥ የከተተው ተግባር በወታደሮቹ ተፈጸመ፡፡ የግብጽ ፀጥታ ኃይሎች ሕፃን ሳይለዩ፤ አዋቂ ሳይመርጡ ንጹሐን ደረት ላይ ቃታ ስበው በራቢዓ እና አልናህዳ ጎዳናዎች ያገኟቸውን ቢያንስ 900 ንጹሐንን ጣሉ፡፡
ይህ ክስተት በጸሐፊዎች የሚጠራው “የራቢዓ ጭፍጨፋ” ተብሎ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 817 ነው ቢልም ጭፍጨፋውን የመሩት የአል ሲሲ አስተዳደር ያቋቋመው መርማሪ ኮሚቴ የሟቾች አሐዝ ከመብት ተሟጋቹ ድርጅት ያነሰ ነው ብሏል፡፡ቁጥሩ ቢለያይም ከሪፖርቱ በኋላ እስካሁንም ድረስ በጭፍጨፋው ላይ የተሳተፈ አንድም ግለሰብ ለፍርድ ቀርቦ ፍትሕ አልሰፈነም፡፡
ከአል ሲሲ ጦር የተረፉ ፍትሕ የናፈቁ ግብጻዊያን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመረጧቸው የነጻነት እና ፍትህ ፓርቲ መሪው፣ መሐንዲሱ፣ ፕሮፌሰሩ እና አምስተኛው የግብጽ ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ሙርሲ በፍርድ ቤት ችሎት ፊት ተዝለፍልፈው ወድቀው ሕይወታቸው ሲያልፍም ተመለከቱ፡፡
አሳዛኙ ክስተት 12 ዓመት ሲደፍን፤ ግብጻውያን የዛሬውን ቀን በዝምታ እያለፉት ነው፡፡ አል ሲሲ በሚመሯት ሀገር አንድም መገናኛ ብዙኃን ክስተቱን በትውስታ ለማንሳትም አይደፍርም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












