በስሩ ካቀፋቸው 57 ሀገሮች መካከል 48 ሙስሊም ሀገራትን ያካተተው የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፤ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አቅራቢነት በፀጥታ ካቢኔው የጸደቀውን ጋዛን ሙሉ በሙሉ በወረራ የመያዝ ዕቅድ አዲስ ባወጣው መግለጫ አውግዟል፡፡ ድርጅቱ እቅዱን “አደገኛና ተቀባይነት የሌለው ጦርነት አባባሽ ነው” ሲል ኮንኖታል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ የድርጅቱ ተወካይ የቱርክ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አሲሊ ጉቨን፤ በኒው ዮርክ ዋና መሥሪያ ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህን አቋም አንጸባርቀዋል፡፡
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት እስራኤል የጋዛን ቀጠና ሙሉ ለሙሉ በወታደራዊ ቁጥጥር ስር ለማዋል የምታደርገውን እንቅስቃሴ “በጽኑ ይቃወማል” ያሉት ተወካዩዋ፤ ርምጃው “ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ በመጣስ እና ሕገ ወጥ ወረራን በኃይል ለማስፈፀም [የሚደረግ] ሙከራ ነው” ብለውታል፡፡
“በጋዛ ቀጠና ላይ የሚካሄደውን በእስራኤል የሚሰነዘረውን ጥቃት በአስቸኳይ እና ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እንጠይቃለን” በማለትም፤ እስራኤል “በአስቸኳይ እና ያለ ቅድመ ሁኔታ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ አቅርቦትን ጨምሮ የሰብዓዊ ርዳታ ወደ ጋዛ ቀጠና እንዲገባ እንድትፈቅድ” ጥሪ ማቅረባቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
በድርጅቱ ውግዘት የገጠመው የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ ያጸደቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድ ባለፈው ሣምንት ጁመዓ ሲጸድቅ፤ አምስት መርሆዎችን መያዙን የእስራኤል ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡ የዕቅዱ ዝርዝር “ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት”፣ “በሕይወት ያሉና የሞቱትን አስከሬን ጨምሮ ሁሉንም ምርኮኞች መመለስ”፣ “ጋዛ ከተማን ከወታደራዊ ትጥቅ ነጻ በማድረግ ከተማዋን የሚያስተዳድረው ሐማስን ማስወገድ” እና “[የእስራኤል ወታደሮች በወረራ የያዙትን] ዌስት ባንክን አስተዳዳሪነት ከፍልስጤም አስተዳደር በማላቀቅ አማራጭ የሲቪል መንግሥት ምሥረታ”ን ያካተተ ነው።
ዕቅዱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት አምባሳደሮች ነቀፌታ ተሰንዝሮበታል፡፡ የኔታንያሁ እቅድ በፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ወቅትም ከባድ ትችት እንደገጠመው የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ እንግሊዝ እና ፈረንሣይን ጨምሮ ሌሎችም ዕቅዱ “ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግን ይጥሳል” ሲሉ በማስጠንቀቅ ከዴንማርክ፣ ግሪክ እና ስሎቬንያ ጋር በመሆን እንዲቀለበስ ጠይቀዋል፡፡ [ሚንበር ቲቪ]












