የምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ጋና፤ የመጀመርያውን አጠቃላይ የእስላማዊ ባንክ እና ፋይናንስ የቁጥጥር ማዕቀፍ ከቀጣይ ዓመት ጥር ወር በፊት ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡
ሀገሪቱ በዘርፉ የቁጥጥር ማዕቀፍ ይፋ ልታደርግ መሆኑን የጋና ማዕከላዊ ባንክ አማካሪ ጆን ጋርትቺ ጋቲ ለኢስላሚክ ፋይናንስ ኒውስ ገልጸዋል፡፡ ይፋ የሚደረገው የቁጥጥር ማዕቀፍ በእስላማዊ ባንክ እና ፋይናንስ ውስጥ ሁሉን አቀፍ አሠራር ለመዘርጋት እንደሚያግዝ የተናገሩት አማካሪው፤ ርምጃው ለሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሐብቶች “በዘርፉ አዳዲስ ዕድሎችን ይከፍታል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የእስላማዊ ባንክ እና ፋይናንስ የቁጥጥር ማዕቀፍ ይፋ ለማድረግ ዝግጅት ላይ በምትገኘው ጋና፤ እ.አ.አ በ2021 በተደረገ የሕዝብ ቆጠራ መሠረት ከአጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ 19 ነጥብ 9 በመቶ ሙስሊም ነዋሪዎችን ይዛለች፡፡ በባንክ አጠቃቀም ረገድ ከጠቅላላው ሕዝብ 42 በመቶው ከአገልግሎት ውጭ መሆኑ ይነገራል፡፡ ሀገሪቱ ከሸሪዓ ተስማሚ የባንክ አሠራር ተግባራዊ ማድረጓ ከባንክ አገልግሎት ከራቀው መካከል ከፊሉን ሊመልስ ይችላል በሚል በጋና ኢኮኖሚ ላይ የሚጽፉ ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ናይጄሪያ የእስላማዊ ፋይናንስን ተግባራዊ ካደረጉ ሀገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ናይጄሪያ ዘርፉን በይፋ ካስጀመረች በኋላ በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከእስያ ገበያዎች መሳብ ችላለች፡፡ የጋና ውሳኔ ተመሣሣይ የኢኮኖሚ ትሩፋት ሊያስገኝ እንደሚችል የሚናገሩ አሉ፡፡
በዓለማችን በርካታ ሀገሮች ውስጥ ስኬታማ መሆኑ በተረጋገጠው እስላማዊ ፋይናንስ፤ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ (በ2023-2024) ሦስቱ የአፍሪካ ትልልቅ ኢኮኖሚዎች ማለትም ናይጄሪያ፣ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ በሱኩክ 3 ነጥብ 045 ቢሊዮን ዶላር ማሰብሰብ ያስቻለ መሆኑን ይፋዊ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ ከሸሪዓ ጋር ተስማሚ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ አራት ባንኮች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ወለድ አልባ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ “አማና ኢንሹራንስ”፤ በአራት ወራት ውስጥ ሥራ የመጀመር ዕቅድ እንዳለው መሥራቾች በዚህ ሣምንት ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ ብቸኛው የሀገሪቱ የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመጀመርያውን ከወለድ ነፃ ቦንድ “ሱኩክ” ሥራ ላይ በማዋል ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሐብት ለማሰባሰብ መዘጋጀቱን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባስጀመረበት መስከረም/2016 ያሳወቀ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












