አውስትራሊያ በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ አማካኝነት በመጪው መስከረም ወር ለፍልስጤም ሉዓላዊ ሀገርነት ዕውቅና እንደምትሰጥ ይፋ አድርጋለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ውሳኔን ማሳለፍ ያስፈለገው በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን “ተደጋጋሚ ጠብ” ለመግታትና “በጋዛ ያለውን ግጭት፣ ስቃይ እና ረሐብ ለማስቆም” መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክሲዮስ የተሠኘው የአሜሪካ የዜና ድረ ገጽ እንደዘገበው፤ የአውስትራሊያ ውሳኔ የተሰማው የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ ከአሜሪካ አቻቸው ማርኮ ሩብዮ ጋር የስልክ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ ሁለቱ ባለሥልጣናት የተነጋገሩት እሑድ እለት ነው፡፡ ይህን መረጃ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አረጋግጧል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ በዎንግ እና ሩብዮ ውይይት ከተነሱ አጀንዳዎች መካከል “የመካከለኛው ምሥራቅ ወቅታዊ ሁኔታ” እና “ፀረ ሴማዊነትን መዋጋት” የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ይሁን እንጂ በውይይቱ አውስትራሊያ ለፍልስጤም እሠጣለሁ ስላለችው የሉዓላዊ ሀገርነት ዕውቅና ጉዳይ ስለመነሳቱ ለማጣራት ያደረግኩት ሙከራ የሀገሮቹ ተወካዮች ምላሽ ባለመስጠታቸው አልተሳካልኝም ሲል የዜና ምንጩ በዘገባው ጠቅሷል፡፡
ከአውስትራሊያ በተጨማሪ ባለፉት ቀናት ፈረንሣይ፣ ካናዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም ለፍልስጤም የሉዓላዊ ሀገርነት ዕውቅና እንደሚሰጡ ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ የሀገራቱን ውሳኔ እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ ተቃውመውታል፡፡
የኒውዚላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊንስተን ፒተርስ፤ ሀገራቸው ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ለመስጠት ዕቅድ መያዟን በተመሣሣይ በዛሬው እለት ገልጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












