Homeዜናና ወቅታዊዜናበኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ የመጀመርያው ወለድ አልባ አገልግሎት ሰጪ በቀጣይ ወራት ሥራ ሊጀምር...

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ የመጀመርያው ወለድ አልባ አገልግሎት ሰጪ በቀጣይ ወራት ሥራ ሊጀምር ነው

በኢትዮጵያ የመጀመርያው ወለድ አልባ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ አማና ኢንሹራንስ፤ በአራት ወራት ውስጥ ሥራ የመጀመር ዕቅድ እንዳለው የኩባንያው መሥራቾች ተናገሩ። በሁለት ወር ውስጥ የመጨረሻውን ፍቃድ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሸሪዓ ሕግጋት ጋር ተስማሚ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው አማና ኢንሹራንስ፣ በሁለት ወር ውስጥ ፍቃድ በማግኘት በቀጣይ አራት ወር ጊዜ ሥራ ሊጀምር መሆኑን የኩባንያው መሥራች አህባቡ ዓብደላ ነግረውኛል ብሎ ያስነበበው ዛሬ ለኅትመት የበቃው ካፒታል ጋዜጣ ነው።

በዘገባው መሠረት ሥራ ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል የተባለው ኩባንያው 83 ባለድርሻዎችን ያቀፈ ነው። ከባለድርሻዎቹ መካከል በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ አራት ባንኮች ውስጥ ሦስቱ ይገኙበታል። እነዚህ ባንኮች ሂጅራ፣ ራሚስ እና ሸበሌ ናቸው። ባንኮቹ ያላቸው የድርሻ መጠን 5 በመቶ ነው። ቀሪው ዘምዘም ባንክ በቴክኒካዊ ችግር ምክንያት በባለድርሻነት መሣተፍ አለመቻሉ በዘገባው ተጠቅሷል።

የአማና ኢንሹራንስ የመጀመሪያ የተከፈለ የካፒታል መጠን 260 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ነው። ይህ መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያስቀመጠው ዝቅተኛው የ400 ሚሊዮን ብር መስፈርት ላይ ባይደርስም ካፒታሉ የተሰበሰበው ከአዲሱ ደንብ በፊት በመሆኑ ኩባንያው መስፈርቱን ለማሟላት ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ጊዜ እንዳለው ተጠቅሷል።

አዲስ መጪው አማና ኢንሹራንስ የሚመራው በዘርፉ ለረዥም ጊዜ ልምድ ባላቸው የቀድሞው የሱዳን ዩናይትድ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሱዳናዊው ዙሃይር ሐሰን ነው።

‘አማና ተካፉል ኢንሹራንስ’ በሚል መጠሪያ የተቋቋመው ኩባንያው፣ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት ሥያሜውን ‘አማና ኢንሹራንስ’ በሚል ተክቷል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular