በስፔን ደቡብ ምሥራቅ በሙርሲያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የጁሚላ ከተማ አስተዳደር፤ የዒድ አልፊጥር እና ዒድ አልአድሓ በዓላት የሲቪክ ማዕከላት እና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ጨምሮ በሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች እንዳይከበሩ እግድ ጣለ፡፡ በወግ አጥባቂው ፒፕልስ ፓርቲ አማካኝነት የቀረበው ይህ ውሳኔ፤ በስፔን እስላማዊ ድርጅቶች ፌዴሬሽን እና በሶሻሊስት ፓርቲ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡
የውሳኔ ሐሣቡን ቀኝ ዘመም አክራሪው ቮክስ ፓርቲ በድምጸ ተዓቅቦ ሲያሳልፈው፤ በግራ ዘመም ፓርቲዎች ተቃውሞ ቢገጥመውም በወግ አጥባቂው ፒፕልስ ፓርቲ አብላጫ ድምጽ መጽደቁን የዘ ጋርዲያን ዘገባ ያመለክታል፡፡
ፒፕልስ ፓርቲ ለሕግ መወሰኛው ባቀረበው የጽሑፍ መግለጫ ላይ፤ የከተማው የስፖርት ማዘውተሪያዎች በአካባቢው ባለሥልጣን ዕውቅና ካልሆነ በስተቀር “ከማንነታችን ጋር ለሚጋጩ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ ወይም ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ አይችሉም” የሚል አስፍሯል፡፡ ሥፍራዎቹ ለእስልምና በዓላት አገልግሎት እንዳይውሉ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ቀኝ ዘመም አክራሪው ቮክስ ፓርቲ ለውሳኔው ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡ ፓርቲው በኤክስ ገጹ፤ ስፔን በሥም የጠቀሰው ሌላ ሃይማኖት “ምድር” መሆኗን በመግለጽ፤ “ለዘላለም በዚሁ ትቀጥላለች” ብሏል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ ለኤል ፓይስ ጋዜጣ ምላሽ የሰጡት የስፔን እስላማዊ ድርጅቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሙኒር ቤንጄሎውን አንደሉሲ፤ “ሐሳቡ አግላይ እና በእስልምናን ጠልነት” የሚመደብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ በተለይ “እስልምና እና ሙስሊሞችን ለብቻ ነጥለው እያጠቁ” መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በቅርብ ጊዜያት በሀገሪቱ “የዘር ጥላቻ ንግግሮች እና ጥቃቶች” መበራከታቸውን በመጥቀስ “[ውሳኔው] በስፔን በ30 ዓመታት [ታሪክ] ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ፍርሐት እንዲሰማኝ አድርጓል” ብለዋል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ውሳኔው የስፔን ሕገ መንግሥት አንቀፅ 16ን የሚፃረር በመሆኑ ይግባኝ ሊቀርብበት የሚችል ነው፡፡ አንቀጹ “የግለሰቦችንና የማኅበረሰቦች የሃይማኖት እና የአምልኮ ነፃነት የተረጋገጠ” መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ላይ ገደብ መጣል እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ ውሳኔውን የተቃወሙት በሙርሲያ የሶሻሊስት መሪ የሆኑት ፍራንሲስኮ ሉካስም በኤክስ ገጽ፤ ፒፕልስ ፓርቲ ያሳለፈው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መሆኑን በማረጋገጥ፤ ፓርቲው “ሥልጣንን አላግባብ በመሻት ማኅበራዊ ትብብርን በቀላሉ አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ አሳልፏል” ብለዋል፡፡
27 ሺሕ ገደማ ነዋሪዎችን ባቀፈችቸው ጁሚላ፤ ከሕዝቧ ውስጥ 7 ነጥብ 5 በመቶ ከሙስሊም ሀገሮች የፈለሠ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












