ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከሐላል ሥጋ የወጪ ንግድ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡ ሳዑዲ ዐረቢያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዋንኛ ሥጋ ተቀባይ ሀገሮች ሆነዋል፡፡
የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሥራት ጤራ ለ“ሚንበር ቲቪ” እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ ከእንስሳት ምርት ወጪ ንግድ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 120 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍየል እና በግ ሥጋ ንግድ የተገኘው 99 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከዳልጋ ከብት እና ግመል ሥጋ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡ ከዳልጋ ከብት እና ግመል የተላከው ሥጋ 1 ሺሕ 478 ቶን ነው፡፡
ምርቱ በዋነኝነት የተላከው ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሀገሮቹ መካከል የሳዑዲ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ከተላከው ምርት 55 በመቶውን ተቀብላለች፡፡ 40 በመቶው የተላከው ወደ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ ኳታርን ጨምሮ ወደ ሌሎች ሀገሮች መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ከበግ፣ ፍየል፣ የዳልጋ ከብት እና ግመል ሥጋ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ተረፈ ምርት ወደ ውጪ ተልኳል፡፡ የኢትዮጵያ የእንስሳት ምርት ወጪ ንግዱ ከባለፈው ዓመት አንጻር 60 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ገልጸዋል፡፡ በገቢ ምንጭ የተመዘገበው ዕድገት 53 በመቶ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከሐላል ሥጋ ጋር በተገናኘ ወደ ውጪ የምትልካቸው ምርቶች የጥራት እና ደኅንነት ማረጋገጫ እንደሚሰጣቸው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህን አገልግሎት በብቸኝነት የሚሰጠው የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ምክር ቤቱ የምርት ጥራት እና ደኅንነት፣ ለእርድ የሚቀርቡ እንስሳት አያያዝ፣ መጓጓዣ እና የእርድ ሥርዐቱን ጨምሮ የሐላል መመዘኛዎችን መሟላቱን ማረጋገጫ ይሰጣል ብለዋል፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ተቆጣጣሪ ተቋማትም ሒደቱ ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል፡፡ እነዚህ ተቆጣጣሪዎች ድንገተኛ እንዲሁም ዓመታዊ ቁጥጥር እንደሚያደርጉም ዶክተር አሥራት ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 120 ሚሊዮን ዶላር ከእንስሳት ምርት ወጪ ማግኘቷ የተገለጸው ኢትዮጵያ፤ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ ትይዛለች፡፡ ከሀገሪቱ የእንስሳት ምርት አንጻር ገቢውን ለማሳደግ በቀጣይ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት አስታውቋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሐላል ሥጋ ትልቁ አስመጪ ሀገር ሳዑዲ ዐረቢያ ስትሆን፤ ማሌዥያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ ኢንዶኔዥያ እና ግብፅ በተከታይነት እንደተቀመጡ የዩሮሚት ኒውስ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ወደ እስላማዊ የትብብር ድርጅት (ኦአይሲ) ሀገሮች 10 የሐላል ሥጋ ላኪዎች 14 ነጥብ 519 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ዋጋ ያለው የንግድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ ወደ እነዚህ ሀገሮች ትልቁ የሐላል ሥጋ ላኪ ሀገር ብራዚል ነች፡፡ አውስትራሊያ፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን፣ ኔዘርላንድ፣ ስፔን፣ ሶማሊያ እና ቱርክ እስከ ዐስረኛ ድረስ ተቀምጠዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












