የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ፤ የባንክ ሥርዐት የማይጠቀሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት “በአፋጣኝ” በባንክ እንዲገለገሉ አሳሰቡ፡፡ ገዥው በተለይ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በትይዩ ገበያ የውጭ ምንዛሬ ገበያ የሚያስፋፉ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ተስተውለዋል ብለዋል፡፡
ገዥው ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጡት የሚመሩት ማዕከላዊ ባንክ ማክሰኞ ሐምሌ 29/2017 በድጋሚ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ካስጀመረ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ጨረታ አንድ የአሜሪካን ዶላር 138 ነጥብ 25 ብር ተሽጧል፡፡
በማብራሪያው ላይ በጨረታው 28 ንግድ ባንኮች ተሳትፈው “የጠየቁትን ያህል የውጭ ምንዛሬ ማግኘታቸውን” የገለጹት ማሞ ምሕረቱ፤ በራሳቸው ካከማቹት ጋር ባንድነት ከዛሬ ጀምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ለንግዱ ማኅበረሰብ ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች በድምሩ 500 ሚሊዮን ዶላር ወርሐዊ አቅርቦት እንዳላቸው በመጠቆም፤ ብሔራዊ ባንክ እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ያቀርባል ብለዋል፡፡ አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚፈልጉ የውጭ መንገደኞችም ከውጭ ምንዛሬ አቅራቢዎች ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ገዥው ከዚሁ ጋር በተገናኘ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የባንክ ሥርዐት የማይጠቀሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት መኖራቸውን በመጠቆም “በአፋጣኝ” በባንክ እንዲገለገሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትይዩ ገበያ የሚዘዋወረውን የውጭ ምንዛሬ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ስለሚከታተል፣ በዚህ ገበያ የሚጠቀሙ ግለሰቦችን ክትትል በማድረግ ገንዘባቸውን መውረስ ድረስ የሚደርስ ርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ከገበያው ባፈነገጠ መልኩ የትይዩ ገበያውን የሚያስፋፉ ድርጊቶች በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ በመስተዋላቸው ይህን በመከታተል ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












