Homeዜናና ወቅታዊዜናብሪታንያ በ1967 የድንበር ስምምነት መሠረት ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ያላትን ድጋፍ አረጋገጠች

ብሪታንያ በ1967 የድንበር ስምምነት መሠረት ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ያላትን ድጋፍ አረጋገጠች

የብሪታንያ መንግሥት በመስከረም ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ፤ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ለመስጠት ባስቀመጠው ዕቅድ ላይ አዳዲስ ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል።

ከፍልስጤም አስተዳደር ጋር በቅርቡ በተፈራረመው የመግባቢያ ሠነድ ላይ ብሪታንያ “በ1967 ድንበር ላይ የተመሠረተ የሁለት ግዛት መፍትሔ” እና “ምሥራቅ ቁድስን ጨምሮ በወረራ የተያዘውን የፍልስጤም ግዛት እንደ እስራኤል አካል ዕውቅና” እንደማይሰጥ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ምሥራቅ ቁድስን ጨምሮ ዌስት ባንክ እና ጋዛ በፍልስጤም አስተዳደር ስር እንደገና መዋቀር ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡

ለፍልስጤም አስተዳደር ድጋፍ በተንጸባረቀበት መግለጫ ላይ በጋዛ በቀጣይ የአስተዳደር፣ የፀጥታ እና መልሶ ማገገም ሥራ ላይ ሚና የጎላ እንዲሆን ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ሚድል ኢስት ዐይ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል የጋዛ አስተዳደር ከሐማስ እንዲወጣና ትጥቅ እንዲፈታ መጠየቃቸውን አስታውሷል፡፡

አሁን በብሪታንያ የቀረበው ሐሳብ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከወራት በፊት ይፋ ያደረጉትን ጋዛን የመቆጣጠር ዕቅድ የሚቃረን ነው፡፡ የብሪታንያ መንግሥት ለፍልስጤም ሉዓላዊ መንግሥትነት በመስከረም ወር ዕውቅና ለመስጠት በዕቅድ መያዙን ያስታወቀው ባለፈው ሣምንት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የሀገሪቱ ውሳኔ የመጣው ፈረንሣይ ተመሳሳይ ርምጃ እንደምትወስድ ካሳወቀች በኋላ ነው፡፡ ፈረንሣይ እና ብሪታንያ ለፍልስጤም ዕውቅና ከሰጡ የመጀመሪያዎቹ የቡድን ሰባት ሀገሮች ይሆናሉ።

ውሳኔውን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ በሰጠው ምላሽ፤ ሀገሪቱ ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠቷን ለሐማስ ሽልማት ነው ብሎታል፡፡

ውሳኔውን የተቃወሙት ኔታንያሁ፤ በሔግ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት በሰብዓዊነት እና በጦር ወንጀሎች የእስር ማዘዣ እንደወጣባቸው ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋነኝነት በጋዛ ውስጥ ረሐብን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

ኔታንያሁ የሚያዙት ጦር ለሁለት ዓመት ገደማ በጋዛ በቀጠለው ጥቃት ቢያንስ 60 ሺሕ ንጹሐን ተገድለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular