በማኅበረሰብ አቀፍ ችግሮች ላይ የሚሠራው ቢላሉል ሐበሺ የልማት እና የመረዳጃ ዕድር፤ በጤና እና ትምሕርት ዘርፎች ላይ አዲስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ ያደረገው የምሥረታውን 25ኛ ዓመት የብር እዮቤልዮ በማስመልከት በተሰጠ መግለጫ ነው፡፡ ድርጅቱ “25 የደግነት ዓመታት” በሚል ሥያሜ ክብረ በዓሉን “በልዩ ልዩ ሁነቶች” ለማክበር በዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡
ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 30/2017 በዋና መሥሪያ ቤት በተሰጠው መግለጫ ላይ፤ የልማት ድርጅቱ እስካሁን የሔደበትን “ሠፊ ማኅበረሰባዊ ችግር የመቅረፍ ሥራ” በመቀጠል የኅብረተሰቡን የጤናና የሕክምና ተደራሽነት ችግር ከመቅረፍ ባሻገር የታዳጊ ወጣቶችን ሕይወት የሚያሻሽሉ” ፕሮጀክቶችን ነድፎ ወደተግባር ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ በኃላፊዎቹ የተጠቀሱት ፕሮጀክቶች የእናቶች እና የሕፃናት ክሊኒክ እንዲሁም የትምሕርት እና ሥልጠና ማዕከላት ናቸው።
ከዚህ ጎን ለጎን የብር እዮቤልዮ አከባበር መርሐ ግብሩ ለተከታታይ ወራት በልዩ ልዩ መሰናዶች እንደሚከበርም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሒደት በሀገር ውስጥ እና ከሀገርም ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን የሚያንቀሳቀሱ “የደግነት ንቅናቄዎች” እንደሚደረጉም ጠቁመዋል፡፡ ተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ይፋ ይደረጉበታል በተባለው በዚህ ዝግጅት ላይ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከልማት ድርጅቱ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቢላሉል ሐበሺ የልማት እና የመረዳጃ ዕድር፤ የሕዝቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት ረዥም ዘመናትን ባስቆጠረው የ“ዕድር” ሀገር በቀል አደረጃጀት የተመሠረተው በ1992 ነው፡፡ ከምሥረታው አንስቶ በወላጅ አጥ ሕፃናት፣ በአቅመ ደካሞች፣ በሱስ ማገገሚያ ማቋቋም፣ በቀብር ማስፈጸም፣ በአቅም ግንባታና የክሕሎት ሥልጠና፣ በሙዝየም አገልግሎት እንዲሁም በትምሕርት እና ሥልጠና ላይ ሲሠራ የቆየ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












