የእስላማዊ ሀገሮች ትብብር ድርጅት እና ዐረብ ሊግ፤ በቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር አታማር ቤን ግቪር ተመርተው ሠፋሪዎች በመስጂደል አቅሷ ላይ እሑድ እለት የፈጸሙትን ወረራ ያወገዙት አዲስ ባወጡት መግለጫ ነው፡፡
ቤን ግቪር ሕገ ወጥ ሠፋሪዎችን እየመሩ እሑድ ጧት ላይ የአይሁዳውያንን በዓል ለማክበር በሚል መስጂዱ ላይ ወረራ ፈጽመዋል፡፡ የዐረብ ሊግ እና የእስላማዊ ትብብር ድርጅት በተናጠል እስራኤል በኮነን ያወጡት መግለጫ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመ “ትንኮሳ” መሆኑንም የሚገልጽ ነው፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት “አለመረጋጋት ሊያስከትል የሚችል” መሆኑን በመጥቀስ፤ “ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችንም ሊያዳክም እንደሚችል” አስጠንቅቀዋል።
ከድርጅቶች በተጨማሪ የሳዑዲ ዐረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ በእስራኤል ባለሥልጣናት የሚፈጸሙ እንዲህ ያሉ ተደጋጋሚ ጥሰቶች በክልሉ ውስጥ ውጥረትን ያባብሳሉ ብሏል፡፡ እነዚህን የሰላም ጥረቶች የሚያዳክሙና ዓለም አቀፍ ሕጎችንና ደንቦችን የሚፃረሩ ተግባራትን ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ ሚኒስቴሩ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።
የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ድርጊቱን በመኮነን ድርጊቱ በመስጂደል አቅሷ ያለውን ሁኔታ ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የጣሰ ነው ሲል ገልጾታል። ዮርዳኖስ በመግለጫዋ የእስራኤል የደኅንነት ሹሙ የመሩት ሠፋሪ ቡድን የደፈረው ግቢ “ለሙስሊሞች ብቻ የተፈቀደ የአምልኮ ሥፍራ” መሆኑንና እስራኤል መብት እንደሌላት አስታውቃለች፡፡
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የቤን ግቪር ድርጊት “አስቀያሚ” እና “የእስራኤልን አክራሪ ባሕርይ የሚያንፀባርቅ” መሆኑን በመግለጽ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም አሜሪካ ይህን እንድታስቆም አሳስበዋል፡፡ በቁድስ የሚገኘው እስላማዊ ወቅፍ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ በቤን ግቪር የሚመሩ 1 ሺሕ 251 ሠፋሪዎች እሑድ ጧት በግቢው ሲደርሱ በከባድ የፖሊስ ጥበቃ ታጅበው ነበር፡፡
በምሥራቅ ቁድስ የሚገኘው መስጂደል አቅሷ እ.አ.አ በ1967 በዓለም አቀፍ ሕግ የፍልስጤም ግዛቶች አካል ሆኖ ዕውቅና የተሰጠው ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች በበመርኮዝ መስጂዱን የምታስተዳድረው ዮርዳኖስ ነች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












