በመካከለኛው አውሮፓ የምትገኘው ስሎቬኒያ፤ በጋዛ ላይ በሚሠነዘረው ጥቃት ሳቢያ ከእስራኤል ጋር የምታደርገውን የጦር መሣሪያ ንግድ በሙሉ በማቋረጥ የመጀመርያዋ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገር ሆናለች፡፡
የስሎቬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ጎሎብ ዕገዳውን ይፋ ያደረጉት ከመንግሥታቸው የካቢኔ ስብሰባ በኋላ ነው፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ “ስሎቬንያ ወደ እስራኤል የጦር መሣሪያዎችን ማስመጣት፣ ወደ ውጭ መላክና ወደ እስራኤል ማጓጓዝ የከለከለች የመጀመሪያዋ የአውሮፓ ሀገር ነች” የሚል አስፍሯል፡፡ ውሳኔውን በተናጠል ያሳለፈችው የአውሮፓ ኅብረት “በውስጣዊ አለመግባባቶች ምክንያት” ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ባለመቻሉ እንደሆነም ገልጻለች፡፡
በጋዛ በቀጠለው የእስራኤል አውዳሚ ጦርነት ሰብዓዊ ርዳታ እንዳይገባ በመከልከሉ ሰዎች እየሞቱ ነው ያለው መግለጫው፤ የሀገሪቱ መንግሥት እ.አ.አ ከጥቅምት 2023 አንስቶ በጋዛ በሚሠነዘረው ጥቃት የጦር መሣሪያዎችን ወደ እስራኤል ለመላክ ምንም ዓይነት ፍቃድ አለመስጠቱንም ጠቁሟል፡፡
ስሎቬንያ በተመሣሣይ በሐምሌ ወር መጀመርያ ላይ ከአውሮፓ ኅብረት ሀገሮች ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት የቀኝ ዘመም አክራሪ የእስራኤል ሚኒስትሮችን ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ መክልከሏንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት ክልከላውን የጣለው ሁለቱ ሚኒስትሮች በፍልስጤማውያን የሰብዓዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እና ከባባድ ጥሰቶች እንዲፈፀም አነሳስተዋል የሚል ክስ ካቀረበ በኋላ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የስሎቬኒያ ፓርላማ አየርላንድ፣ ኖርዌይ እና ስፔንን በመከተል ለፍልስጤም ግዛት እውቅና የሚሰጥ ድንጋጌ ማጽደቁ የሚታወቅ ነው፡፡
እስራኤል ጋዛ ላይ ለ22 ወራት ያህል የከፈተችውን ጦርነት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችና የተባበሩት መንግሥታት ባለሞያዎች በዘር ፍጅት ፈርጀውታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












