ንባብ ለሕይወት ከኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ጋር በጥምረት ያዘጋጁት የ“ንባብ ለሕይወት” የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተው ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 24/2017 ነው፡፡
ዐውደ ርዕዩ በይፋ ሲከፈት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ፣ የመሰናዶውን ጠቀሜታ በማጉላት በመላው ሀገሪቱ የንባብ አብዮት ማስጀመር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የንባብ ባሕል በተለይ ሕፃናትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በዐውደ ርዕዩ ላይ የልጆች፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የፖለቲካ፣ እስላማዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንዲሁም ትምሕርታዊ መጻሕፍት ቀርበዋል። አንጋፋው የአዲስ አበባ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ እና ነጃሺ ማተሚያ ቤት በዐውደ ርእዩ ላይ ከተሳተፉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በርካታ ደራሲያን በተከታታይ ይታደሙበታል ተብሎ የሚጠበቀው መድረክ፤ ከዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 24/2017 እስከ ሐምሌ 27/2017 ድረስ ይቆያል፡፡ ነባር መጻሕፍት ለሽያጭ ከመቅረባቸው ባሻገር አዳዲስ መጻሕፍት ምርቃት ሥነ ሥርዐት ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ አዘጋጆቹ ገልፀዋል። (ሚንበር ቲቪ)












