Homeዜናና ወቅታዊዜናየቀድሞ የብሪታንያ ዲፕሎማቶች ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሣይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንዲሰጡ...

የቀድሞ የብሪታንያ ዲፕሎማቶች ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሣይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንዲሰጡ ጠየቁ

26 የቀድሞ የብሪታንያ ዲፕሎማቶች ያካተተ ቡድን፤ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት እውቅና እንዲሰጡ ጥሪ ያቀረቡት በታይምስ ጋዜጣ ላይ ባስነበቡት ደብዳቤ ነው፡፡

በበርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች የቀድሞ የብሪታንያ አምባሳደሮች የተፈረመው ደብዳቤ ላይ በቱርክ የቀድሞ አምባሳደር ሰር ዶሚኒክ ቺልኮት፣ በሊቢያ የቀድሞ አምባሳደር ፒተር ሚሌት እና በሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር የነበሩት ሎርድ አንድሪው ግሪን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ሀገራቸው ለፍልስጤም እውቅና እንዲሰጥ የሚጠይቀው ደብዳቤ፤ በአፍጋኒስታን የቀድሞው አምባሳደር ሰር ዊሊያም ፓቴይ እንዲሁም ፒተር ጄንኪንስ፣ ሰር ጄረሚ ግሪንስቶክ እና ሎርድ ዴቪድ ሃኔ የተባሉ የተባበሩት መንግሥታት የቀድሞ አምባሳደሮችም ፊርማ ያረፈበት ነው፡፡

የዲፕሎማቶቹ ደብዳቤ የመጣው የፈረንሣይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንግሊዝን ለመጎብኘት በተዘጋጁበት ወቅት ነው፡፡ ማክሮን እንግሊዝ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቀው ዛሬ ማካሰኞ ነው፡፡ ዲፕሎማቶቹ፤ ስታርመር እና ማክሮን “በጋዛ ውስጥ አፋጣኝ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም” እንዲደረግ በድጋሚ ግፊት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

አክለውም ሁለቱ መሪዎች “የፍልስጤምን መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” እውቅና ለመስጠት አሁን መወሰን እንዳለባቸውና ፍልስጤሞች ከእስራኤል ጎን ለጎን ስለ ራሳቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው አስፍረዋል፡፡

ባለፈው ወር ፈረንሳይ ከሳዑዲ ዐረቢያ ጋር በመሆን በጋራ በኒውዮርክ ባዘጋጀችው ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት እውቅና ለመስጠት ዝግጅት ማድረጓ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ ይሁንና ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ በጉባኤው ላይ ፈረንሣይ ዕውቅናውን ባትሰጥም ዩናይትድ ኪንግደም ለፍልስጤም እውቅና እንድትሰጥ የማግባባት ሥራ ሠርታለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular