አቢሲንያ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት፤ በአቢሲንያ አሚን በኩል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና መምህራን የሚያዘጋጀው ‘አሚን ስኩል አዋርድ’ የተካሔደው ዛሬ እሑድ ሰኔ 29/2017 ነው፡፡
ባንኩ ሽልማቱን ያበረከተው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው በነጃሺ አካዳሚ ነው። በሽልማት ሥነ ሥርዐቱ ላይ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የአቢሲንያ አሚን የብራንድ አምባሳደር ሙሐመድ ፈረጅ ተገኝተዋል።
ባንኩ በነጃሺ አካዳሚ የገንዝብ ሽልማት ያበረከተላቸው ተማሪዎች ከየክፍል እርከኑ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ሽልማቱ የተበረከተላቸው ተማሪዎች ከ5ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ለሚገኙት አራት ሺሕ ብር ሲሆን፣ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ደግሞ ሰባት ሺሕ ብር ነው።
በሽልማት ሥነ ሥርአቱ ላይ ከየክፍል እርከኑ አንደኛ ከወጡ ተማሪዎች ውጪ፤ ከሁሉም ክፍሎች ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበው ተማሪ በልዩ ሁኔታ የ10 ሺሕ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ከአቢሲንያ አሚን ተበርክቶለታል፡፡
ከተማሪዎች በተጨማሪ የላቀ አፈጻጸም ለነበራቸው ለሶስት መምህራንም ሽልማት አበርክቷል፡፡ በአቢሲንያ አሚን ለመምህራኑ አስር ሺሕ ብር ተበርክቷል።
በሽልማት ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የአቢሲንያ ባንክ አቢሲንያ አሚን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ፕሮዳክት ዲቪዥን ማናጀር አቶ ሙሐመድ አሰፋ፣ አቢሲንያ አሚን ሸሪዓን ማዕከል ባደረገ መልኩ የሥራ ዕድል ከመፍጠርና ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን ከመወጣት አንጻር ሀገራዊ ተልዕኮውን በተሳካ ሁኔታ እየተወጣ መቀጠሉን ገልጸዋል። የሽልማት መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን የትምህርት ዕድገት ለመደገፍ፣ ልህቀትን ለማጎልበት እና ብቁ ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት ያለመ መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም ተሸላሚዎቹ ለሀገራዊ የትምህርት ዕድገት እና ለትውልድ ዕውቀት መሠረት ብርታት ለመሆን የበለጠ እንዲተጉ እንዲሁም ለወደፊቱ ለሀገር፣ ለቤተሰብ እና ለትምህርት ቤታቸው ኩራት እንዲሆኑ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቢሲንያ አሚን የሚያዘጋጀው አሚን ስኩል አዋርድ በተመሳሳይ በትላንትናው ዕለት በኮርዶቫ እና ረዛን ትምህርት ቤቶች በ2017 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና መምህራን የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡
አቢሲንያ አሚን በአዲስ አበባ ከተማ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በሌሎች የክልል ከተሞች በአጠቃላይ በዘጠኝ ትምህርት ቤቶች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ለተማሪዎችና መምህራን የሚያበረክተውን የማበረታቻ ሽልማት እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሽልማት የተበረከተላቸው ተማሪ ወላጆች በበኩላቸው፤ ባንኩ ያበረከተው ሽልማት ለቀጣይ መንገድ ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል፡፡ የተማሪ ወላጆችም እንዲሁ ሽልማቱ ተማሪዎችን ውጤታማነት ከማስጠበቁ ባሻገር ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሽልማቱ የተበረከተላቸው መምህራን አቢሲኒያ አሚን በትምህርት ዘርፍ እየሠራ የሚገኘው ሥራ እጅግ በጣም የሚደነቅ መሆኑን በመጥቀስ ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳቸው እንደሚሆንም ተናግረዋል።
አቢሲንያ ባንክ ከ2011 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎቹን ወደ ሥራ በማስገባት በአሁኑ ጊዜ ከ69 በላይ የሚሆኑ ቅርንጫፎች በመላው ኢትዮጵያ በመክፈት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ባንኩ አሁን ያለውን አሠራር በማዘመን፣ ዘመኑን የሚመጥን የዲጂታል ግብይት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ደንበኞቹን በተሻለ ለማገልገል የሚያስችሉ ከወረቀት ነፃ የሆኑ አገልግሎቶችን በሥራ ላይ አውሏል፡፡ (ሚን












