የአል ነጃሺ መስጂድ ዕድሳት መጠናቀቁን የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ) የገለፀው ዛሬ ጁመዓ ሰኔ 27/2017 ነው። ድርጅቱ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መረጃ፣ ታሪካዊው መስጅድ ዓለም አቀፍ የክብር፣ የሰላም እና የመሸሸጊያነት ትዕምርት ነው ብሏል።
የአል ነጃሺ መስጂድ ዕድሳት የተጀመረው መስከረም 13/2017 ነበር። የዕድሳት ሥራው የተከናወነው በትግራይ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርገው በቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ አማካኝነት ነው፡፡ ሥራው በዋነኝነት በሁለቱ አካላት ትብብር የተከናወነ ቢሆንም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንዲሁም የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ተሳታፊ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

የግንባታውን ወጪ የሸፈነው የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ፤ በሀገሪቱ የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኝ የልማት መምሪያ ነው፡፡
ዕድሳቱ መጠናቀቁ የተገለፀው አል ነጃሺ መስጅድ፤ ከትግራይ ክልል ዋና መቀመጫ መቐለ ከተማ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በአራት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው አል ነጃሺ መስጅድ፤ ዋናውን መስጂድ እንዲሁም ሁለት የቀብር ሥፍራዎችን በውስጡ ይዟል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












