Homeዜናና ወቅታዊዜናበፓርላማ፡ የነዳጅ ታክስ፣ የሕዝብ ቆጠራ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት እና...

በፓርላማ፡ የነዳጅ ታክስ፣ የሕዝብ ቆጠራ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት እና የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ

የኢፌዴሪ ፓርላማ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 24/2017 ባካሔደው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 41ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ የፌዴራል መንግሥት የ2018 ረቂቅ በጀት ላይ ባስቀመጠው መሠረት፤ ከነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች 15 በመቶ ቫት በማስከፈል ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመንግሥት የተቀመጠው ከነዳጅ የሚሰበሰበው ታክስ “አዲስ አለመሆኑን” ያነሱት አቶ አሕመድ፤ “በዚሁ ምክር ቤት ቀርቦ የነበረ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አፈጻጸሙን በተመለከተም በቀጣይ የበጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይደረግ አልያም የምጣኔው ግማሽ ይሰብሰብ የሚለው “እስካሁን ውሳኔ ያላገኘ” ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም፤ “የሚመለከታቸው አካላት በጋራ የሚያዩት ነው” ሲሉ በቀጣይ ውሳኔ እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥት አቅጣጫ መቀመጡን ያረጋገጡት ሚኒስትሩ፤ በትግበራው “የዓለም የነዳጅ ዋጋና የድጎማ መጠኑ እየታየ ለወደፊት በሚሰጥ አቅጣጫ የሚስተናገድ” መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው በዚህ ውሳኔ ምክንያት “በአሁኑ ሰዓት የሚከተል የነዳጅ ጭማሪ የሌለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል” ብለዋል፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች የቀረበው የ2018 የፌዴራል መንግሥት በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1.93 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ ከ2018 ረቂቅ በጀት 1.2 ትሪሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 415 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ፣ 315 ቢሊዮን ብር ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲሁም 14 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ድጋፍ የሚውል ነው።

በዛሬው እለት በተካሄደው የፓርላማ ውሎ ከነዳጅ በተጨማሪ የክልሎች በጀት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እቅድ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራን በማንሳት አቶ አሕመድ ሽዴ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ መንግሥት በቀጣይ ዓመት ምርጫ ስለሚደረግ ቆጠራውን ለማድረግ በጀት አለመያዙን በመጠቆም፤ “ቀጣዩ በጀት ዓመት ሲጠናቀቅ” ሊደረግ የሚችል መሆኑንም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርላማው የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን አዋጅ እንዲሁም የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular