መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው በድር ኢትዮጵያ፤ የዘንድሮ ጉባዔውን ነገ ሐሙስ በካናዳ ቶሮንቶ ሊጀምር መሆኑ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ ለ25ኛ ጊዜ በሚያካሔደው ጉባዔ ላይ ለመታደም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ወደ ሥፍራው አምርተዋል፡፡
ድርጅቱ ያሠራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ጉባዔው ነገ ሐሙስ ሰኔ 26/2017 ተጀምሮ እስከ እሑድ ሰኔ 29/2017 ለአራት ቀናት የሚቀጥል ነው፡፡ በካናዳ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ዝግጅት የሚያስተባብረው በቶሮንቶ የሚገኘው ነጃሺ ኢስላማዊ ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ የዘንድሮው ጉባዔ በሒልተን ሆቴል እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡
በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያ፣ ከሰሜን አሜሪካ እንዲሁም ከተለያዩ ሀገሮች የሚጓዙ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከኢትዮጵያ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ ዓብዱልከሪም በድረዲን፣ ዋና ጸሐፊው ሸይኽ ሐሚድ ሙሳ እና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ባልደረባው ኡስታዝ ሱፍያን ዑስማን ትናንት ምሽት ቶሮንቶ መግባታቸው ታውቋል፡፡
ድርጅቱ በድረ ገጹ ባሠራጨው መረጃ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ኢብራሂም ቱፋ እንደሚሳተፉ የገለጸ ቢሆንም ትናንት ቶሮንቶ ከደረሰው የጠቅላይ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች ልዑክ ጋር አልታዩም፡፡ እስካሁን ድረስ መሳተፍ አልያም አለመሳተፋቸውም አልተገለጸም፡፡

የዓመታዊው ጉባዔ አዘጋጅ በድር ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ፣ ካናዳ እና አውሮፓን ጨምሮ 27 የሙስሊም ማኅበረሰብ አባላትን የሚወክል ድርጅት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 24ኛ ጉባኤ “እስላማዊ መርሆች ላይ ፀንቶ መቆም” በሚል መሪ ቃል በአሜሪካ ዳላስ አከናውኗል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ማከናወኑም ይታወሳል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












