Homeዜናና ወቅታዊዜናትራምፕ በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ በይፋ ትእዛዝ አስተላለፉ

ትራምፕ በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ በይፋ ትእዛዝ አስተላለፉ

አሜሪካ በቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሻር አል አሰድ አገዛዝ ዘመን የጣለችው ማዕቀብ እንዲሻር የሚጠይቀው ትዕዛዝ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ ትራምፕ ፊርማውን ያኖሩት ትናንት ሰኞ ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ በሶሪያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ የሚሽረው ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው በግንቦት ወር ሳዑዲ ዐረቢያን በጎበኙበት በልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን አመቻችነት ከሶሪያ ፕሬዝዳንት አሕመድ አሸረዕ ጋር ለጥቂት ደቂቃ በሪያድ ውይይት ካደረጉ በኋላ ማዕቀቡ እንደሚነሳ የገቡትን ቃል ያከበሩበት ሆኗል፡፡

ማዕቀቡን የሚሽረው ሰነድ ፊርማ ከተካሄደ በኋላ የተናገሩት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮሊን ሌቪት፤ ውሳኔው ሀገሪቱ ወደ መረጋጋት እና ሰላም የምታደርገውን ጉዞ ወደፊት ለማራመድ እና ለመደገፍ የሚደረግ ጥረት አካል ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ትዕዛዙ በሶሪያ ላይ [እንደ ሀገር] የተጣለውን ማዕቀብ ቢያነሳም በቀድሞው ፕሬዝዳንት በሻር አል አሰድና ተባባሪዎቻቸው፣ የሰብአዊ መብቶችን በተላለፉ፣ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን፣ ከኬሚካል የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች እና የኢራን ወኪሎች ላይ ጸንቶ እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡  

ትዕዛዙን የፈረሙት ትራምፕ “የተረጋጋች፣ የተዋሐደችና ከራሷና ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም የምትኖር ሶሪያን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነን” ብለው ነበር፡፡

የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ ተከትሎ የሶሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሰድ ሻባኒ ሀገራቸው በአዎንታዊ እንደምትቀበለው በኤክስ ገጽ ላይ አስፍረዋል፡፡ ሻባኒ፤ “ውሳኔው ሶሪያን ወደ አዲስ የብልጽግና፣ የመረጋጋት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ክፍት ወደ መሆን የሚያራምድ ወሳኝ ርምጃ” እንደሆነ ጽፈዋል፡፡

ውሳኔው የሶሪያ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ዋና ዋና እንቅፋቶችን በማስወገድ፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የመልሶ ግንባታ እና የልማት በሮችን የሚከፍት መሆኑን በመግለጽ፤ ወሳኝ የመሠረተ ልማት መልሶ ግንባታ፣ የተፈናቀሉ ሶሪያውያን ወደ ሀገራቸው በክብር እንዲመለሱ ጥርጊያ መንገድ የሚያመቻች መሆኑንም አክለዋል፡፡

አሜሪካ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የአሁኑ የሶሪያ ፕሬዝዳንት አሕመድ አሸረዕ፤ ቀድሞ ሐያት ተሕሪር አሻም የተሰኘው ቡድን መሪ በነበሩት ወቅት አግኝቶ ላስረከበ 10 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እንደምትሰጥ በማሳወቅ ከተፈላጊዎች ዝርዝር ስር የነበሩ ቢሆንም፤ ቡድናቸው ደማስቆን ከተቆጣጠረ በኋላ ይህ ማዘዣ በአሜሪካ እንዲሻር ተደርጓል፡፡ ትራምፕ ከአሕመድ አሸረዕ ጋር በሳዑዲ በተገናኙበት ወቅት ጠንካራ ነው ላሏቸው አሕመድ አሸረዕ መልካም ምኞት ገልጸውላቸው ነበር፡፡

አሕመድ አሸረዕ የሚመሩት ሐያት ተሕሪር አልሻም ደማስቀን ተቆጣጥሮ የአሳድን ሥርወ መንግሥት የጣለው በታኅሣሥ ወር ነበር፡፡ ቡድኑ ከተማዋን ከመቆጣጠሩ አስቀድሞ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሻር አል አሰድ ወደ ሞስኮ መኮብለላቸው የሚታወስ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular