Homeዜናና ወቅታዊዜናየባንኮች 18 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያ እስከ ቀጣዩ የመስከረም ወር ድረስ...

የባንኮች 18 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያ እስከ ቀጣዩ የመስከረም ወር ድረስ ባለበት “እንዲቆይ” ውሳኔ ተላለፈ

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ፤ 18 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያ እስከ ቀጣዩ የመስከረም ወር ድረስ ባለበት እንዲቆይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየወሰደ ያለው “ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲም እንዲቀጥል ወስኗል፡፡

ኮሚቴው ይህን የገለጸው ዛሬ ሰኔ 23/2017 ካካሄደው ሦስተኛ ስብሰባ በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ ኮሚቴው በስብሰባው በዋጋ ግሽበት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የገንዘብ ሁኔታ፣ የወለድ ተመን ሁኔታ፣ የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፣ የፊስካል ሁኔታ፣ የባንክና ፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት እና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይት ማካሄዱ ተገልጿል፡፡

በኮሚቴው መግለጫ መሠረት፤ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መጥቶ በሚያዝያ እና በግንቦት ወር 2017 መጨረሻ 14.4 በመቶ ደርሷል፡፡ የዋጋ ግሽበትን ተከፋፍሎ ሲታይ፤ ምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት ግንቦት ወር 2017 መጨረሻ 12.1 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 25.6 በመቶ ጋር ሲነጻጸር “ከፍተኛ ቅናሽ” አሳይቷል፡፡

በተመሳሳይ ወቅት 17.8 በመቶ የደረሰው ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ “ከቅርብ ወራት ወዲህ በተወሰነ መልኩ እያንሰራራ ይገኛል”፡፡ ለዚህም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አካባቢ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጫና “በተወሰነ መልኩ አስተዋጽኦ ማድረጉ” ተጠቅሷል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲንከባለል የመጣው የዋጋ ግሽበት አሁን ካለበት ደረጃ በይበልጥ መውረድና የኑሮ ውድነትም “በኅብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ያለው ከባድ ጫና መቅለል እንዳለበት”ና ይህንንም ግብ ለማሳካት ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበሩን መቀጠል እንደሚገባው ኮሚቴው መረዳቱ በመግለጫው ላይ ሠፍሯል፡፡

በዚህም “አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት የመርገብ አዝማሚያ ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ” በሥራ ላይ ያለው 18 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣራ እስከ ቀጣዩ የመስከረም ወር 2018 የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ጊዜ ድረስ እንዲቆይ ተወስኗል፡፡

በሌላ በኩል የባንኮች የብድር ዕድገት ገደብ በመስከረም ወር 2018 እንደሚከለስ ታሳቢ የተደረገ ቢሆንም፣ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት የመርገብ አዝማሚያ ባስጠበቀ መልኩ የሚደረጉ ለውጦች ወዳልተፈለገ ልል የገንዘብ ፖሊሲ እንዳያመራ ብሔራዊ ባንክ እንደ አስፈላጊነቱ ገበያ-መር የሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን እንደሚጠቀም ገልጿል፡፡

እነዚህ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች “የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመንን”፤ “ከባንኮች ጋር የሚደረግ የገንዘብ ግብይትን”፣ “የውጭ ምንዛሬ መሸጥ ወይም መግዛትን” እንዲሁም “ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡትን የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ መለወጥን” ያካትታሉ ተብሏል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ለማስቻል እነዚህ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎች “እንደ አስፈላጊነቱ በተናጠል ወይም በቅንጅት ጥቅም ላይ እንዲውሉ” ይደረጋል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ቀጣዩ ስብሰባ መስከረም ወር 2018 መጨረሻ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚያ ቀደም ብሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular