የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በመዲናዋ በበይነ መረብ የሚሰጠው የ2017 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ዛሬ ሰኞ ሰኔ 23/2017 እንደተጀመረ ገልጿል፡፡
በቢሮው መረጃ መሠረት ፈተናው በከተማ አስተዳደሩ በ108 የማስፈተኛ ጣቢያዎች ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በዛሬው የመጀመሪያ ዙር ፈተና ከ13 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ለፈታው ተቀምጠዋል፡፡
ፈተናው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቀደም ሲል ተማሪዎቹ የልምምድ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉን እና በቂ ኦረንቴሽን መሰጠቱ እንዲሁም በየመፈተኛ ጣቢያው መሰረተ ልማቶቹን ዝግጁ የማድረግ ሥራን ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየቱንም አስታውሷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ዴታ ከወይዘሮ አየለች እሸቴ እና ከምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ዲናኦል ጫላ ጋር በመሆን ፈተናው ከሚሰጥባቸው ጣቢያዎች መካከል በአብረሆት ተገኝተው የፈተናውን አጀማመር ተመልክተዋል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከ280 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 51 ሺሕ 259 የተፈጥሮ እና የማኅበራዊ ሣይንስ ተማሪዎች በአራት ዙር የ2017 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












