ሕንድ በፓኪስታን ሦስት ግዛቶች በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት በሦስት መስጂዶች ላይ ውድመት መድረሱ ተሰምቷል፡፡ ሀገሪቱ ጥቃቱን የሰነዘረችው ባሃዋልፑር፣ ኮትሊ እና ሙዛፋራባድ በተባሉ ግዛቶች እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
ኢስላሚክ ኢንፎርሜሽን እንደዘገበው ከሆነ፤ ባሃዋልፑር ውስጥ የሚገኘው ሱብሃነላህ የተሰኘ መስጂድ ቀዳሚ የሚሳኤል ጥቃት አርፎበታል፡፡ በመስጂዱ ላይ ውድመት የደረሰው የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር “ኦፕሬሽን ሲንዶር” በሚል በጠራው ዘመቻ ነው፡፡ በመስጂዱ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ስድስት አንድ ሕጻንን ጨምሮ ሰዎች ሲገደሉ በርካታ ምዕመናን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ጥቃቱ መስጂዱን ከማውደሙ በተጨማሪ በአቅራቢያው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ከፍርስራሽ ስር ማውጣታቸውን የዓይን እማኞች መናገራቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በመስጂዱ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት የፓኪስታን ሠራዊት ቃል አቀባይ ሌተናል አሕመድ ሸሪፍ ማረጋገጣቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ በአጠቃላይ በጥቃቱ ውድመት የደረሰባቸው መስጂዶች ብዛት ሦስት ነው፡፡ በመስጆዶች ላይ ውድመት የደረሰው በባሃዋልፑር አሕመድፑር ሻርቂያ ከተማ፣ በኮትሊ እና ሙዛፋራባድ ነው፡፡ በአሕመድፑር ሻርቂያ በመስጂድ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በመጠን ከፍተኛ እንደነበር የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ የሦስት ዓመት እድሜ ያላት ሕጻን መገደሏንም በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ በቀሪዎቹ ሁለት አካባቢዎች የ16 ዓመት እድሜ ያላት አንዲት ሴትና የ18 ዓመት ወጣት ወንድ ግድያ እንደተፈጸመባቸው አክለዋል፡፡
ከጥቃቱ በኋላ የፑንጃብ አውራጃ ባለሥልጣናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣል የፀጥታ አካላት እና ሆስፒታሎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ዛሬ ረቡዕ ትምህርት ቤቶችም ዝግ ተደርገዋል፡፡
ሕንድ ዘመቻውን የከፈተችው በዚህ ወር አጋማሽ የተገደሉ ሕንዳውያን እና አንድ ኔፓላዊ የገደሉ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚል መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ሕንዳውያን ጎብኚዎችን በቀጠፈው ጥቃት ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት የገለጸችው ፓኪስታን፤ የሕንድ የሚሳኤል ጥቃት ምክንያት የለሽ መሆኑን አሳውቃለች፡፡ በሚሳኤል ጥቃቱ በአጠቃላይ ስምንት ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል ሲል የሀገሪቱ መካላከያ ኃይል አሳውቋል፡፡ በጥቃቱ 35 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ማስተናገዳቸውን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ የፓኪስታን ኢስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሸሪፍ፤ “ፀያፍ” ሲሉ ለጠሩት ትንኮሳ “ምላሽ ሳይሰጠው የሚታለፍ” አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው ሕንድ በፓኪስታን ላይ የፈጸመችው ወታደራዊ ጥቃት አሳስቦኛል ብለዋል፡፡ ዓለም የሁለቱን ሀገሮች ወታደራዊ ግጭት የመቋቋም አቅም የለውም ሲሉ በቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱጃሪች በኩል ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም እንዲሁ የሕንድ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ የሰማነው ነገር አሳዛኝ ነው ሲሉ ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡
ፓኪስታን እና ሕንድ በ1947 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ ወዲህ ለሦስት ጊዜ በሙሉ ኃይል ጦርነት ገጥመዋል፡፡ ሁለቱም የኒኩለር ቦምብ የታጠቁ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












