የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በዘንድሮ ዓመት ለሚከናወነው ሐጅ ላይ ለክንውኑ የተዘጋጀውን ቪዛ ያልያዙ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን በሥነ ሥርዐቱ ላይ ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከሐጅ ቪዛ ውጭ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመሳተፍ ሙከራ ማድረግ “ብዙ መዘዝ” ሊያመጣ የሚችል መሆኑንም ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ይህን ያስታወቀው በሐጅ ኦፕሬሽን ሲስተም ተጠሪው አንዋር ሙስጠፋ በኩል ነው፡፡ አንዋር ይህን የተናገሩት ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለዘንድሮው ሐጅ እስካሁን ድረስ ያከናወናቸውን ሥራዎች በተመለከተ ከሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዐብዱልፈታህ ሙሐመድ ጋር በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የሐጅ ምዝገባ የሚከናወነው በጠቅላይ ምክር ቤቱ በኩል ብቻ መሆኑን ያስታወሱት የሲስተም ተጠሪው፤ ለዘንድሮ ዓመት የተቀመጠው የምዕመናን ኮታ ምዝገባ የተከናወነውም በዚሁ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ቀድሞ ከተቀመጠው ኮታ ጭማሪ ሊኖር እንደማይችል በመጠቆም፤ በጠቅላይ ምክር ቤቱ ሥርዐት የማያልፉ ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ በሌሎች የቪዛ ዐይነቶች ሊገቡ ቢችሉም ከፍተኛ እንግልት ሊያስተናግዱ እንዲሁም “ብዙ መዘዝ” ሊከተላቸው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የሐጅ ቪዛ ያልዙ ምዕመናን ወደ መካ ከተማ ማለፍ እንደማይችሉ የተናገሩት አንዋር፤ በሐጅ ላይ ለመሳተፍ ከሐጅ ቪዛ በተጨማሪ ምዕመናን የተዘጋጀውን መታወቂያ ካርድ በእጅ ማስገባት ርግጠኛ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡ ለሑጃጅ የሚዘጋጀው የመታወቂያ ካርድ ኑሱክ የተሰኘ መሆኑን የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም አሳውቋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤት በተያዘው ዓመት በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመሳተፍ ወደ ቅዱሳኑ ከተሞች ይጓዛሉ በሚል ያስቀመጠው የምዕመናን ቁጥር ስድስት ሺሕ ነው፡፡ የምክር ቤቱ የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዐብዱልፈታህ ሙሐመድ ይህን ቁጥር ታሳቢ ያደረገ ምዝገባ ሲካሄድ መቆየቱን አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ቁጥር አምና ከተጓዙት ምዕመናን በግማሽ ያነሰ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ኃላፊዎች ከዚህ ቀደም እንዳሳወቁት፤ ኮታው እንዲቀንስ ያስገደደው በኢትዮጵያ በዶላር እና በብር መካከል ባለው ምጣኔ ላይ በተደረገው ጭማሪ ምክንያት ነው፡፡
በክንውኑ ላይ የሚሳተፉ ምዕመናን ከአዲስ አበባ በመነሳት መዲና ከተማ እንደሚያርፉ የተገለጸ ሲሆን፣ የመልስ ጉዞ ከጂዳ የሚነሳ እንደሚሆን የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር፤ ምእመናንን መቀበል በጀመረበት ጊዜ ፍቃድ ያልያዙ ሑጃጅ ላይ እስራት እና የገንዘብ መቀጮ እንደሚጥል አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን ባሳወቀበት መግለጫው፤ ፍቃድ ሳይኖራቸው ማጭበርበር ይፈጽማሉ ያላቸው ላይ ቅጣቱን የደነገገው፤ ቀድሞ ለሐጅ ክንውን ባስቀመጠው ደንብ መሠረት ተፈጻሚ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይፋ በተደረገው ደንብ በቅዱሳኑ ከተሞች ያለፍቃድ ከተገኙ ምዕመናን በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ላይ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡
በዚህም ያልተፈቀደላቸው የሐጅ ምዕመናንን የሚያጓጉዙ ላይ፤ ለእያንዳንዱ ጥሰት የ15 ቀናት እስራት ቅጣት እንዲጣል ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም በእያንዳንዱ ፍቃድ ያልያዘ ተሳፋሪ 10 ሺሕ የሳዑዲ ሪያል የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ተሳፋሪዎች በቁጥር ሲጨምሩ ቅጣቱም ከፍ የሚል ይሆናል፡፡
ድርጊቱን በተደጋጋሚ እንዳይከሰት አጥፊዎች በአደባባይ እንዲታዩ ይደረጋል ያለው ሚኒስቴሩ፤ የፈጸሙት የውጭ ሀገራት ዜጎች ከሆኑ ቅጣት ካጠናቀቁ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ደግመው እንዳይገቡ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ዘንድሮ ሐጅ ማከናወን የሚችሉት ሕጋዊ ቪዛ የሚይዙ ብቻ እንደሆኑ ምዕመናን በድጋሚ እንዲያውቁት ሲል አሳስቧል፡፡ የሐሰት ሠነድ በመጠቀም የተያዘ ማንኛውም ሰው በሕጉ መሠረት በቁጥጥር ስር ውሎ ለፍርድ እንደሚቀርብ በማሳሰብ፤ ለዑምራ ክንውንም ሆነ ሌሎች የቪዛ ዐይነቶችን መስጠት ማቆሙንም ከዚህ ቀደም አሳውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት በሐጅ ሥነ ሥርአት ክንውን ላይ ከመላው ዓለም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












