Homeዜናና ወቅታዊዜናከመጪው ሰኔ ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ፓስፖርት ለማውጣት “እንደ ዋንኛ...

ከመጪው ሰኔ ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ፓስፖርት ለማውጣት “እንደ ዋንኛ ሠነድ” ሊጠየቅ ነው

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፤ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ከሰኔ 1/2017 ጀምሮ ፓስፖርት ለማውጣት እንደ ዋንኛ ሠነድ መጠየቅ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ አገልግሎቱ ይህን ያስታወቀው ከዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ጋር መረጃዎችን መጋራት የሚያስችል አሠራር ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች የዲጂታል አሠራርን በተመለከተ በአርባ ምንጭ ከተማ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በመግለጫው እንደተናገሩት፤ ከሰኔ 1 ጀምሮ ዲጂታል መታወቂያ እንደ ዋንኛ ሠነድ ሆነ ያገለግላል፡፡ መታወቂያው ዋና ሠነድ ተደርጎ የሚጠየቀው ከሌሎች ሠነዶች በተጨማሪነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ያጸደቀው መጋቢት 21/2015 ነበር፡፡ ለፓስፖርት እንደ ዋና ሠነድ ይጠየቃል የተባለው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) አንድን ሰው በልዩ ሁኔታ መለየት የሚያስችል እንደሆነ ይገለጻል፡፡ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም እንዳወጣው መረጃ፤ መታወቂያው ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰዎችን የተመጠነ ግላዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርኅ እያንዳንዱን ዜጋ በልዩ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው፡፡

ሥም፣ ፆታ፣ የትውልድ ቀን እና የመኖሪያ አድራሻ በፋዳ መታወቂያ ይካተታሉ። በተጨማሪም ባዮሜትሪክ የሚባለው መረጃ ማለትም የሁለት የዓይን፣ የዐስሩም የእጅ ጣቶች እና የፊት አሻራንም የሚይዝ ነው፡፡ መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ተጨምቆ ወደ 12 አሐዝ ልዩ ቁጥር እና ወደ 16 አሐዝ ተለዋጭ ቁጥር ተቀይሮ ለተመዝጋቢው ይሰጣል፡፡

በኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጁ አንቀፅ 16 (1) መሠረት፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የአንድን ሰው ማንነት ለማረጋገጥ እንደ ሕጋዊ እና በቂ ማስረጃ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ደንግጓል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular