ዩናይትድ ኪንግደም በመጪዎቹ ክረምት ወራት ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ለመስጠት ከፈረንሣይ እና ሳዑዲ ዐረቢያ ጋር ውይይት እያካሔደች እንደምትገኝ ተዘግቧል፡፡ ይህንኑ የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ፤ ከሁለት ቀን በፊት ለሀገሪቱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና መከላከያ ኮሚቴ ባቀረቡት ንግግር አረጋግጠዋል፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም ይህ ዕቅድ የተሰማው በሰኔ ወር በአሜሪካ ኒውዮርክ ከሚካሔደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ አስቀድሞ ነው፡፡ ቀደም ብለው በወጡ ዘገባዎች እንደተገለጸው፤ በከተማዋ የሚካሔደውን ጉባኤ የሚያዘጋጁት ፈረንሣይ እና ሳዑዲ ዐረቢያ ናቸው፡፡ ይህ ጉባኤ የፍልስጤም እና እስራኤልን ግጭት የማስቆም ዓላማ ያዘለ መሆኑን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡
ይህ የዩናይትድ ኪንግደም ዕቅድ ይፋ የተደረገው፤ የፈረንሣዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቀጣይ ወራት ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ሊሰጡ እንደሚችሉ ከተናገሩ ከሦስት ሳምንት በኋላ ነው፡፡ ማክሮን በወቅቱ ከ‘ፍራንስ 5’ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሀገራቸው ዕውቅናውን ልትሰጥ የምትችለው በሰኔ ወር ሊሆን እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተው ነበር፡፡
ከቴሌቭዥን ጣቢያው ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ወደ ዕውቅና መሄድ ይኖርብናል፤ በሚቀጥሉት ወራት ይህን ተግባራዊ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ውሳኔውን የሚያሳልፉት “ማንንም ለማስደሰት” ሳይሆን “ትክክል በመሆኑ” የሚደረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አሁን ዕውቅና ትሰጣለች የተባለችውን የዩናይትድ ኪንግደምን በተመለከተ የተናገሩት የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ፤ በአሁኑ ወቅት 148 ሀገራት ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና መስጠታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ዩናይትድ ኪንግደም ይህን ርምጃ ለመውሰድ የፈለገችው እንዲሁ ዕውቅና ለመስጠት ያክል አለመሆኑን በመግለጽ፤ መሬት ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ዓላማ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው ‘አንዳንድ’ ሲሉ የጠሯቸው የአውሮፓ ሀገሮች “ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና መስጠታቸው” ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አላሳደረም በሚል ነቀፌታ ሰንዝረዋል፡፡
ፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደም የፍልስጤምን ሀገረ መንግሥት በይፋ ካጸደቁ፤ በሁለት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ዘንድ የተሰጠ የመጀመሪያው ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 193 አባል ሀገሮች መካከል 147ቱ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ሰጥተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዐሥሩ የአውሮፓ ሀገሮች ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












