Homeዜናና ወቅታዊዜናየፓኪስታን የግል የሐጅ ወኪሎች የሑጃጅ ክፍያ ገንዘብ ወደተሳሳተ አካውንት ተላልፏል መባሉን “መሠረተ...

የፓኪስታን የግል የሐጅ ወኪሎች የሑጃጅ ክፍያ ገንዘብ ወደተሳሳተ አካውንት ተላልፏል መባሉን “መሠረተ ቢስ ነው” ሲሉ አንድ የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣን አጣጣሉት

የፓኪስታን የግል የሐጅ ወኪሎች የሑጃጅ ክፍያ ገንዘብ ወደተሳሳተ አካውንት ተላልፏል መባሉን “መሠረተ ቢስ ነው” ሲሉ ያጣጣሉት፤ አንድ ሥማቸው ያልተጠቀሰ በሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሠሩ ባለሥልጣን ናቸው፡፡ ባለሥልጣኑ የሀገሪቱ የሐጅ ኤሌክትሮኒክ ሥርዐት “በአስተማማኝ ብቃት እና ግልጽነት” የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የፓኪስታን መገናኛ ብዙኃን ይዘው በወጡት ዘገባ፤ ለዘንድሮ ዓመት ከሀገሪቱ በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመሳተፍ በግል የጉዞ ወኪሎች የተመዘገቡ ምዕመናን ክፍያ በስሕተት በዓለም የነዳጅ ላኪዎች ማኅበር (ኦፔክ) አካውንት እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ ይኸው ጉዳይ በፓኪስታን ፓርላማ ቀርቦ ጥያቄ ማስነሳቱን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ ተፈጥሯል በተባለው ስሕተት ምክንያት 67 ሺሕ ሑጃጅ በክንውኑ ላይ መሳተፋቸው ጥርጣሬ ውስጥ ወድቋል ተብሏል፡፡

ዐረብ ኒውስ እንደዘገበው፤ የተፈጠረው ስሕተት ከገንዘብ ማስተላለፍ ጋር የሚገናኝ ሳይሆን፣ “ስምምነቶችን ቀድሞ በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ባለመፈጸም” የተከሰተ መሆኑን የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡ በሳዑዲ ዐረቢያ እና በፓኪስታን መካከል የስምምነት ውል የተፈረመው ቀድሞ እንደነበር ያስታወሱት ባለሥልጣኑ፤ መንግሥታዊው የፓኪስታን የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር በውሉ መሠረት “ሁሉንም ስምምነት ያለምንም ችግር በተሳካ ሁኔታ ሲያጠናቅቅ”፤ በርካታ የግል ኩባንያዎች ግን በተቀመጠው ጊዜ ሳይፈጽሙ ቀርተዋል፡፡

የፓኪስታን የግል የሐጅ ወኪሎች ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይፋዊ የሐጅ ክፍያ አካውንት መግባት ነበረበት ያሉት የገንዘብ መጠን 60 ሚሊዮን የሳዑዲ ሪያል ነው፡፡ ጉዳዩ በፓርላማ ቀርቦ ውይይት በተደረገበት ወቅት የተናገሩት የፓኪስታን ብሔራዊ ጉባኤ የሃይማኖት ጉዳዮች ሰብሳቢ ማሊክ አሚር፤ የተፈጸመውን ስሕተት በፓኪስታን የሐጅ ታሪክ ውስጥ “እጅግ አስከፊው ቅሌት ነው” ብለውት ነበር፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ሸሕባዝ ሸሪፍን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩ እንዲጣራ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡ የግል ወኪሎች ማኅበር ተወካይ ጉዳዩ በፓርላማ በተሰማበት ወቅት የፓኪስታን የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር “ለመንግሥት ወኪሎች ያደላ አሠራር በመዘርጋት የግል ወኪሎች ላይ በደል ፈጽሟል” የሚል ውንጀላ አቅርበዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በሐጅ ለሚሳተፉ የፓኪስታን ዜጎች የተሰጠው ኮታ 179 ሺሕ 210 ነው፡፡ ሀገሪቱ በጥር ወር ከሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ 90 ሺሕ ምዕመናን በመንግሥት አማካኝነት ለመጓዝ ሲደለደሉ፤ ቀሪው ለግል ወኪሎች የተሰጠ ነበር፡፡ በተፈጠረው የአሠራር ክፍተት በግል ወኪሎች ሊጓዙ የሚችሉት 23 ሺሕ ምዕመናን ብቻ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

በፓኪስታን ይህ ችግር ቢፈጠርም ለዘንድሮ ዓመት ሐጅ ሥነ ሥርዐት በመንግሥት ማእቀፍ የተመዘገቡ ምዕመናን የመጀመሪያ ጉዟቸውን በዚህ ሳምንት ማድረግ ችለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular