በፈረንሳይ ጋኽ ክልል ሌ ግራኽ ኮምቤህ መንደር በሚገኘው ሃቲጄ መስጂድ ውስጥ፤ አቡበከር ሲሴ የተባለ የ24 ዓመት ወጣት ላይ የተፈጸመው ግድያ በሀገሪቱ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ ፍራንስ 24 እንደዘገበው፤ ግድያው የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት ጁመዓ ነው፡፡
ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ ወጣቱን በያዘው ስለት ደጋግሞ በመውጋት ከገደለው በኋላ፤ ድርጊቱን በተንቀሳቃሽ ስልኩ ካሜራ በመቅረጽ በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ አጋርቶታል፡፡ ግለሰቡ ዘግናኙን ድርጊት በካሜራው ሲያስቀር እስልምናን የሚያንቋሽሽ ፀያፍ ንግር ሲያሰማ እንደነበር በደኅንነት ካሜራ ተይዟል፡፡ የወጣቱ አስከሬን የተገኘው ምዕመናን በእለቱ ለጁመዓ ሰላት ወደ መስጂድ በገቡበት ወቅት መሆኑም ታውቋል፡፡
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ብሩኖ ጉታዩ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፤ ግለሰቡ ግድያውን በመፈጸም በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ባጋራው ቪድዮ ላይ ሌሎች ሰዎችን የመግደል ፍላጎት እንዳለው ዛቻ ሲያሰማ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ በሌ ግራኽ ኮምቤህ፤ የድርጊቱ መፈጸም ያስቆጣቸው ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች በአደባባይ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ሰልፈኞቹ በሀገሪቱ በሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግር በተደጋጋሚ እንደሚሰነዘር በማስታወስ፤ ይህ መቆም እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ዘ ፍሬንች ካውንስል ኦፍ ሙስሊም ፌዝ ድርጊቱን ማውገዝ ባወጣው መግለጫ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ሙስሊሞች ዙሪያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዘግየት ብለው በኤክስ ገጽ ባሰፈሩት ድርጊቱን የሚኮንን ጽሑፍ፤ ፈረንሳይ ለዘረኝነት እና ጥላቻ ሥፍራ የላትም ብለዋል፡፡ አክለውም የአምልኮ ነጻነት ሊጣስ እንደማይገባው በመግለጽ፤ “የእኛ” ሲሉ ከጠሯቸው ሙስሊም ዜጎች ጎን እንደሚቆሙም ገልጸዋል፡፡
ገዳዩ ካመለጠ በኋላ ለማደን የሚደረገውን ምርመራ ሲመሩ የቆዩት ዐብዱልከሪም ግሪኒ፤ ኦሊቨር ኤ እንደሚባል የገለጹት ተጠርጣሪ ለድርጊቱ መነሻ የሆነው በአዕምሮው ያዳበረው በእስልምና ላይ ያለው ጥላቻ አንደኛው ሊሆን እንደሚችል በመናገር፤ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ፖሊስ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ የቦስኒያ የዘር ግንድ እንዳለውም ገልጿል፡፡ ግለሰቡ ግድያውን ከፈጸመ በኋላ ማምለጡ ቢነገርም የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ ሰኞ ይዘዋቸው በወጡ ዘገባዎች በጣሊያን በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በፈረንሳይ ድንጋጤ የፈጠረው የግድያ ወንጀል በአልዝሃር ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ ተቋሙ እሑድ ባወጣው መግለጫ፤ ድርጊቱ ሽብር መሆኑን በመግለጽ የነጭ የበላይነትን የሚሰብኩ ቡድኖች በአውሮፓ እና አሜሪካ የሚፈጽሙት ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንም ጠቁሟል፡፡ መግለጫው ይህን የሽብር አዝማሚያ ለመከላከል እና ሙስሊሞችን ከጥቃት ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ የደኅነት ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡
ፈረንሳይ ከአጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ ዘጠኝ በመቶ ሙስሊም ነዋሪዎችን ይዛለች፡፡ ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ2019 በወጣ ሪፖርት ከጠቅላላ ሙስሊም ማኅበረሰቡ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት ‘በሃይማኖታችን ምክንያት መገለል ይደርስብናል’ የሚል እምነት አላቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












