Homeዜናና ወቅታዊዜናአሜሪካ በየመን የስደተኞች ማዕከል በሰነዘረችው የአየር ጥቃት ኢትዮጵያውያን ጉዳት እንደደረሰባቸው ተዘገበ

አሜሪካ በየመን የስደተኞች ማዕከል በሰነዘረችው የአየር ጥቃት ኢትዮጵያውያን ጉዳት እንደደረሰባቸው ተዘገበ

የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላዊ እዝ በሰሜን ምዕራብ የመን ክፍል በስደተኞች ማዕከል ላይ በሰነዘረው የአየር ጥቃት ኢትዮጵያውያን ጉዳት እንደደረሰባቸው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ሬውተርስ የዜና ወኪል አካባቢውን የሚያስተዳድረው ሑውሢ (በይፋዊ መጠሪያው አንሳሩላህ) የተሰኘው ቡድን ቴሌቪዥን ጣቢያ ይዞት የወጣውን ተንቀሳቃሽ ምስል ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አንድ ግለሰብ ከጥቃቱ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ደርሰው ወደ ቃሬዛ ሲያወጡት በአማርኛ ቋንቋ “እናቴን” የሚል ቃል ሲያወጣ ተደምጧል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊ ስደተኛ መሆኑ መለየቱን ዘገባው ጠቅሷል፡፡

ጥቃቱ የተሰነዘረበት ማዕከል ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ለስደት ሲያቋርጡ በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ስር የዋሉ ስደተኞች ማቆያ መሆኑ ተነግሯል፡፡ አሜሪካ ስደተኞችን ባስጠለለው ማዕከል ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት፤ ቢያንስ 68 ሰዎች መገደላቸውን የአንሳሩላህ ልሳን ነው የተባለው አልመሲራህ ቲቪ ዘገባ ያመለክታል፡፡  

የቴሌቪዥን ጣቢያው ባሠራጨው ቪድዮ ጣሪያው ከፈራረሰ መጋዘን መሣይ ቤት ውስጥ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አስከሬን ከፍርስራሾች ውስጥ በቃሬዛ ተሸክመው ሲያወጡ ያሳያል፡፡ ጣቢያው ያናገራቸው የሕክምና ባለሞያ ከሟቾች በተጨማሪ ጥቃቱ የተሰነዘረባቸው ሰዎች የተለያየ የአካል ክፍል ጉዳት ማስተናገዳቸውን አስረድተዋል፡፡

የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው የጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አብዛኞቹ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ፣ አናዶሉ ኤጀንሲ እና አልጀዚራ በተናጠል ያወጡት ዘገባ ያመለክታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጥቃቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ በቃል አቀባዩ ስቴፈን ዱጃሪክ በኩል “ማዘኑን” በመግለጽ፤ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች “የሲቪሎችን ደኅንነት መጠበቅን ቅድሚያ እንዲሰጡ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕጎችን በሙሉ እንዲያከብሩ” ጥሪ አቅርቧል፡፡

አንሳሩላህ በበኩሉ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን ይወስዳል ያለውን የአሜሪካን ጦር ድርጊት አውግዟል፡፡ ጥቃቱን በማድረስ ውንጀላ የቀረበበት የአሜሪካ ወታደራዊ ማእከላዊ ዕዝ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ከመስጠት እንደተቆጠበ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ እዙ ባለፉት ሳምንታት በሰነዘረው ተደጋጋሚ ጥቃት ከ250 በላይ ሰዎች መገደላቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ማእከላዊ ዕዙ ጥቃቱን የሚሰነዝረው የሑውሲ ቡድን ይዞታ ናቸው ባላቸው ሥፍራዎች ላይ መሆኑን በመጥቀስ ሲካላከል መቆየቱንም ዘገባዎቹ አመልክተዋል፡፡

ቡድኑ እስራኤል በጋዛ የሰብዓዊ አቅርቦት ማቋረጧን በመቃወም የሚታወቅ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular