Homeዜናና ወቅታዊዜናየአሜሪካው ዋሺንግተን ግዛት ለሁለቱ ኢስላማዊ በዓላት ዕውቅና ሰጠ

የአሜሪካው ዋሺንግተን ግዛት ለሁለቱ ኢስላማዊ በዓላት ዕውቅና ሰጠ

የአሜሪካ ዋሽንግተን ግዛት ለሁለቱ ኢስላማዊ በዓላት ዕውቅና የሰጠው አዲስ የቀረበውን የሕግ ረቂቅ ባጸደቀበት ወቅት ነው፡፡ በሕጉ ዕውቅና ያገኙት የዒድ አልፊጥር እና ዒድ አል አድሓ በዓላት ናቸው፡፡

የሕግ ረቂቁ በረመዳን ወር የመጨረሻ ቀን በግዛቱ ምክር ቤት በመጽደቁ፤ የግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ ቦብ ፈርጉሰን ማክሰኞ እለት ፊርማቸውን አኑረውበታል፡፡ አስተዳዳሪው ፊርማቸውን ያኖሩበት መድረክ የተዘጋጀው በኢስላሚክ ሴንተር ኦፍ ታኮማ መሆኑን ዋሺንግተን ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ነዋሪነታቸው በሥፍራው ያደረጉ በርካታ ምዕመናን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ቦብ ፈርጉሰን ፊርማውን ባኖሩበት ሥነ ሥርዐት፤ የሚያስተዳድሩት ግዛት ለሁለቱ በዓላት ዕውቅና በመስጠት ቀዳሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ፤ በዓላቱ ዕውቅና እንዲያገኙ ለምክር ቤት የቀረበው በሬድሞንድ ከተማ ተወካይ ዑስማን ሰላሁዲን አማካኝነት ነው፡፡ የሕጉን መጽደቅ ተከትሎ የተናገሩት ዑስማን፤ ሕጉ በሀገሪቱ ተግባራዊ ሲደረግ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን በማስታወስ፤ ውሳኔውን “ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው” ብለዋል፡፡

በርካታ በግዛቱ የሚኖሩ ሙስሊሞች ከእምነታቸው እና ከሞያዊ ኃላፊነታቸው አንደኛውን የመምረጥ ግዴታ ውስጥ ይገቡ እንደነበር በመግለጽ፤ በዚሁ ምክንያት በተለይ በትምሕርት ቤቶች ፈተና እና የምርቃት ሥነ ሥርዐት ከበዓል ቀን ጋር በሚገጥሙበት ወቅት ከዝግጅቱ የመቅረት እንዲሁም ተማሪዎች የሚጣልባቸውን ቅጣት መጋፈጥ ይጠበቅባቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በአዲሱ ሕግ መሠረት ማንኛውም ሠራተኛ በሁለቱ ኢስላማዊ በዓላት ደመወዝ የማይከፈልበት ሁለት የረፍት ቀን መውሰድ ያስችለዋል፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ በላይ ያሉ የትምሕርት ተቋማትም በእነዚህ ቀናት የሚሰጧቸውን ፈተናዎች እለቱን ከግንዛቤ እንዲያስገቡ ግዴታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተማሪዎችም የፈተና ቀናት የጊዜ ሠሌዳ ማስተካከያ እንዲጠይቁ መብት ይሰጣል፡፡

በዋሺንግተን ግዛት የዒድ አልፊጥር እና ዒድ አል አድሓ በዓላትን የሚያከብሩ 100 ሺሕ ሙስሊሞች እንደሚኖሩ አስተዳዳሪው ቦብ ፈርጉሰን ገልጸዋል፡፡ በግዛቱ ከሁለቱ ኢስላማዊ በዓላት በተጨማሪ የደም ልገሣ ቀን፣ የውሐ ደኅነነት ቀን እና የኮሪያ አሜሪካ ቀን ደመወዝ ሳይከፈልባቸው ረፍት መውሰድ ከሚቻልባቸው ቀናት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular