የፈረንሣይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ ሀገራቸው ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት በቅርቡ እውቅና ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረዋል፡፡ ማክሮን ይህን የተናገሩት ፈረንሣይ እና ሳዑዲ ዐረቢያ ከሚያዘጋጁት የፍልስጤም እና እስራኤልን ግጭት ለማስቆም ይካሔዳል ከተባለው ጉባዔ አስቀድሞ ነው፡፡
ከፍራንስ 5 ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ሀገራቸው በቀጣይ ወራት ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት እውቅና እንደሚሰጡ ጥቆማ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ፤ ትክክለኛው ጊዜ ሰኔ ወር ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ከቴሌቭዥን ጣቢያው ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ወደ እውቅና መሄድ ይኖርብናል፤ በሚቀጥሉት ወራት ይህን ተግባራዊ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ አክለውም ውሳኔን ያሳለፉት “ማንንም ለማስደሰት” ሳይሆን “በተወሰነ መልኩ ትክክል በመሆኑ” የሚደረግ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዚህ አስተያየት፤ ከአንድ ዓመት የፍልስጤምን ሀገረ መንግሥት እውቅና ስለመስጠት ሲናገሩ የሰጡትን ፍንጭ ያጸኑበት መሆኑን የሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ ያመለክታል፡፡ በወቅቱ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት እውቅና መስጠት “ለፈረንሣይ ክልክል አይደለም” ያሉት ማክሮን፤ እንዲህ ዐይነቱን ርምጃ መውሰድ “ከሞራል እና ፖለቲካ” አንጻር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ የተናገሩት የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫርሰን አጋቤኪያን ሻሂን፤ ፈረንሣይ ይህን ማድረጓ የፍልስጤምን ሕዝብ መብት በማስጠበቅ ረገድ የተላለፈ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአንጻሩ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር፤ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት እውቅና መስጠት “ለሐማስ ይበልጥ አቅም የሚሰጥ ነው” ሲሉ ተቃውመውታል፡፡
ፈረንሣይ እና ሳዑዲ ዐረቢያ የፍልስጤም እና እስራኤልን ግጭት ለመፍታት ያለመ ነው የተባለውን ጉባኤ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት እንደሚያዘጋጁ ይፋ የተደረገው፤ በዚህ ሣምንት በካይሮ በተካሔደው የግብጽ፣ ፈረንሣይ እና ዮርዳኖስ መሪዎች የሦስትዮሽ ውይይት ወቅት ነው፡፡ ማክሮን ለዚህ ውይይት ወደ ካይሮ በማምራት ከግብጹ ዓብዱልፈታህ አልሲሲ እና ከዮርዳኖሱ ንጉሥ ዐብደላህ ጋር መክረው ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 193 አባል ሀገሮች መካከል 147 ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት እውቅና ሰጥተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዐሥሩ የአውሮፓ ሀገሮች ናቸው፡፡ በመጨረሻው እውቅናውን የሰጡት ስፔን፣ አየርላንድ እና ኖርዌይ ናቸው፡፡ ዩክሬን፣ አልባኒያ፣ ሰርቢያ፣ ሞንቴኔግሮ እና ቤላሩስን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሀገሮች በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ፈረንሣይ ዕውቅና የምትሰጥ ከሆነ 11ኛዋ ሀገር ትሆናለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












