በፓኪስታን በዘንድሮ ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ ለመሳተፍ በግል ወኪሎች የተመዘገቡ ከ77 ሺሕ በላይ ምዕመናን ጉዞ ተደናቅፏል፡፡ ተሳትፎው የተደናቀፈው የግል ወኪሎቹ ቀድሞ “በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ በመቅረታቸው” መሆኑ ተገልጿል፡፡
የግል ወኪሎቹ ለፓኪስታን ከተቀመጠው 179 ሺሕ 210 ኮታ እንዲያስፈጽሙ የወሰዱት የ89 ሺሕ 810 ምዕመናንን የጉዞ ሒደት ድርሻ እንደነበር ዐረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ሆኖም የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ሳያሟሉ በመቅረታቸው ለሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር የጉዞ ማረጋገጫ የሰጠው ለ12 ሺሕ 500 ምዕመናን ብቻ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ አጣሪ ኮሚቴ በማቋቋም ጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ለተቋቋመው ኮሚቴ ማብራሪያ የሰጡት የፓኪስታን የሃይማኖት ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶክተር አጣዑ ረሕማን፤ የግል የጉዞ ወኪሎች ከሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ጋር በታኅሣሥ ወር የተገባውን ስምምነት ጥሰዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተገባው ስምምነት መሠረት ከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ በአንድ ወር ጊዜ ወኪሎቹ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የክፍያ ገንዘብ ያስተላልፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ የሚጠበቀውን ሙሉ ክፍያ ሳይፈጽሙ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተጠናቋል፡፡ በዚህም የሑጃጅ የጉዞ ዕቅድ ተደናቅፏል፡፡ የሀገሪቱ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር የጊዜ ገደቡ ለተጨማሪ ቀናት እንዲራዘም በድጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን የተናገሩት ዶክተር አጣዑ ረሕማን፤ በሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ተቀባይነት አለማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
በሐጅ ክንውን ላይ የሚሳተፉ የፓኪስታን ዜጎች ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የመጀመሪያውን ጉዞ የሚያደርጉት ከሦስት ሣምንት በኋላ ሚያዝያ 23/2017 እንደሚሆን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ከግል የጉዞ ወኪሎች በተጨማሪ በመንግሥት በኩል ለሐጅ የሚጓዙት ፓኪስታናውያን ቁጥር 89 ሺሕ ናቸው፡፡
በ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ ለመሳተፍ ከመላው ዓለም ሀገሮች ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ 10 ሺሕ ምዕመናንን ለመመዝገብ ኮታ ማስቀመጡን ከዚህ ቀደም አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ የተቀመጠው ኮታ እስካሁን ድረስ ተሟልቶ ምዝገባ ስለመጠናቀቁ ይፋ ያደረገው መረጃ የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












