Homeዜናና ወቅታዊዜናከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ምንዛሬ ረገድ “ግምታዊ አስተሳሰቦች” መታየት በመጀመራቸው ጥንቃቄ እንዲደረግ...

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ምንዛሬ ረገድ “ግምታዊ አስተሳሰቦች” መታየት በመጀመራቸው ጥንቃቄ እንዲደረግ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ምንዛሬ ረገድ “ግምታዊ አስተሳሰቦች (ማለትም expectations)” መታየት በመጀመራቸው “ጥንቃቄ እንዲደረግ” ያሳሰበው፤ የባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሁለተኛ ስብሰባውን ካደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 16/2017 የተደረገውን ስብሰባ ተከትሎ የወጣው መግለጫ፤ ኮሚቴው የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል ፖሊሲ ትግበራ፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና ፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ላይ ግምገማ እንደተካሄደ የሚገልጽ ነው፡፡  

በግምገማው መሠረት ከውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ጋር በተያያዘ በተለይም በውጭ ምንዛሬ ተመን ከቅርብ ጊዜ ግምታዊ አስተሳሰቦች (ማለትም expectations) መታየት መጀመራቸውን መገምገሙን የገለጸው ኮሚቴው፤ ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥር ስለሚችል ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘ መታየት የጀመረው ግምታዊ አስተሳሰብ ከሚያስከትላቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች መካከል ዋንኛው የዋጋ ግሽበት “እንዲያንሰራራ ግፊት መፍጠር” በመሆኑ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚቴው በየካቲት ወር 15.0 በመድረስ ቅናሽ አሳይቷል ያለው የዋጋ ግሽበት፤ በቀጣይ ባለት ወራት “ትርጉም ባለው መልኩ” እስኪቀንስ ድረስ አሁን ያለው የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ተገቢ በመሆኑ ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የገንዘብ መጠን በገንዘብ ፖሊሲው ላይ ያልተፈለገ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር መጠንቀቀቅ እንደሚያሻ አሳስቧል፡፡

ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ አሁንም ድረስ በከፍተኛና መካከለኛ ጊዜ “ሊደረስበት ከታሰበው የነጠላ አሐዝ በላይ” በመሆኑ አሁንም ቢሆን “ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ” መከተል አስፈላጊ መሆኑን ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡

ይህ የኮሚቴው መግለጫ “የባንክ ዘርፍ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ ነው” ሲል ያትታል፡፡ ይሁን እንጂ “አንዳንድ ባንኮች” በተወሰነ መልኩ የጥሬ ገንዘብ እከል (liquidity) እጥረት እንደሚታይባቸው አመላክቷል፡፡ ለዚህ መነሻ ሆኗል ያለው በተወሰኑ ባንኮች ዘንድ የብድርና የተቀማጭ ሒሳብ ጥመርታ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን የባንክ ለባንክ ግብይት እና በብሔራዊ ባንክ በኩል ቋሚ ብድር መጀመራቸው “የአንዳንድ ባንኮች ችግር እየተቀረፈ” እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በሰኔ 2017 ቀጣይ ስብሰባውን እንደሚያካሄድ የተገለጸው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው፤ ቀጣዩን የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔ ወደፊት በሚከሰቱ የዋጋ ግሽበት ውጤቶች ላይ የተመሠረተ እንደሚሆንም ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ የተቋቋመው በተሻሻለው የባንኩ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025 አንቀጽ 23 መሠረት መሆኑ ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular