የሶማሌ እና የአፋር ሕዝቦች የወንድማማችነት መድረክ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 16/2017 እንደሚጀምር የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ መድረኩ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ሕዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሚደረግ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የመድረኩ ቅድመ ምክክር ከክልሎቹ የተውጣጡ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት እንደተካሔደ የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል። በመድረኩ ላይ የተናገሩት የሰላም ሚኒስትር ሙሐመድ ኢድሪስ፤ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች የጋራ ታሪክ እንዳላቸው በማስታወስ በጋራ የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል ተብሏል፡፡
አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑንም የተናገሩት ሚኒትሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ የሚካሔደው የወንድማማችነት መድረክ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መፍትሔ በመስጠት መግባባትንና የጋራ ልማትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በተያዘው የረመዳን ወር የአፋር እና ሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ልዑክ በጅግጅጋ እና ሰመራ ከተሞች የኢፍጣር መርሐ ግብር መካሔዱ ይታወሳል፡፡
ከአንድ ሣምንት በሰመራ ከተካሔደው የአፋር እና የሶማሌ ወንድማማች ሕዝቦች ኢፍጣር በኋላ የጻፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ ክልሎቹ በመካከላቸው የነበሩ አለመግባባቶችን እና ደም ያፋሰሱ ግጭቶችን በማቆም “በወንድማማችነት መርሕ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ከስምምነት ደርሰው እጅ ለእጅ በመያያዝ ቃል የተጋቡበት ደማቅ ምሽት ሆኖ አልፏል” ሲሉ ገልጸው ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












