በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት በቤይ ኤሪያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ የሆነው ‘የቤይ ኤሪያ ሙስሊም ኢትዮጵያን ማኅበር’ (Ethiopian Bay Area Muslims Association – EBAMA)፤ ባለፈው ዓመት መጨረሻ የወደመበትን ማዕከል በድጋሚ ለማቋቋም የድጋፍ ማሰባሰብ በይፋ አስጀምሯል፡፡
ማኅበሩ የድጋፍ ማሰባሰቡን በይፋ ያስጀመረው በዚህ ሣምንት ነው፡፡ እ.አ.አ ከ2001 አንስቶ ከ20 ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የዕውቀት እና የተርቢያ ማዕከል በመሆን ያገለገለው ማዕከሉ፤ “በድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ” ውድመት የደረሰበት ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2016 (ሴፕቴምበር 5/2024) ነው፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ያለ ማዕከል መቅረታቸውን በሥፍራው የሚኖረውና በማኅበሩ የግሎባል ፈንድ ሬዚንግ አስተባባሪ የሆነው ገጣሚ ኑረዲን ኢሳ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግሯል፡፡
እንደ አስተባባሪው ከሆነ፤ ማዕከሉ በተለይ በዲን ጉዳይ በዋነኝነት በሕፃናት ላይ ትኩረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ለዚሁ ተግባር ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ በተደረጉ ኡስታዝ፤ የቂርኣት ፕሮግራም እንዲሁም ሣምንታዊ የዳዕዋ ፕሮግራም ያዘጋጅ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ሕፃናት የቁርኣን ጥናት ሲያጠናቅቁ ሌሎች ደግሞ ሒፍዝ ቀጥለዋል፡፡
ከዲን ተግባራት በተጨማሪ ሴቶች እና አረጋዊያን ማኅበራዊ ግዴታዎችን የሚወጡበት ማዕከሉ፤ የረመዳን ኢፍጣር ፕሮግራም እና ዘላቂ የቀብር ሥፍራ አገልግሎት የሚሠጥ ነበር፡፡ በአሜሪካ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በኢትዮጵያ በማኅበራዊ ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉ ተፈጥሮአዊ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ምላሽ መስጠትን የሚያካትት ነው፡፡

የእሳት ቃጠሎው መነሻ በምርመራ ላይ የሚገኘውን ማዕከል በአሁኑ ሰዓት በድጋሚ በማቋቋም አገልግሎቱን ለማስቀጠል የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራሙ ይፋ ሲደረግ፤ በአጠቃላይ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ኑረዲን ተናግሯል፡፡ በአጠቃላይ ከሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን በአባላት መዋጮ እስካሁን ድረስ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር እንደተሰበሰበ በመግለጽም፤ ይፋ የተደረገው ዘመቻ ቀሪውን መጠን ለማሰባሰብ በማቀድ የተደረገ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ በሚሰበስበው ገንዘብ በአሁኑ ሰዓት የማኀበሩ ኃላፊዎች በአቅራቢያ በሚገኝ ሥፍራ ለገበያ የቀረበውን ቤተክርስትያን የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ ሣምንት ይፋ የተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ በኦንላይን ገንዘብ መሰብሰቢያው ‘ጎ ፈንድ ሚ’ የሚደረግ መሆኑን የገለጸው አስተባባሪው፤ ሜይ 5/2025 ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማሰብሰብ ፕሮግራም እንደሚያዘጋጅ ጠቁሟል፡፡ ይህ የድጋፍ ማሰባሰብ በ“ሚንበር ቲቪ” ዋና አስተባባሪነት የሚደረግና ለስድስት ሰዓታት በተከታታይ የሚቆይ እንደሚሆንም ተናግሯል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ላይ “በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ሙስሊም ማኅበራት፣ በሌሎችም ዓለማት የሚገኙ የሙስሊም ጀመዓዎች ምላሽ እንዲሰጡ” ጥሪ አቅርቧል፡፡
የቤይ ኤሪያ ሙስሊም ኢትዮጵያን ማኅበር (EBAMA)፣ በቤይ ኤሪያ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ለማገልገል የተመሠረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። (ሚንበር ቲቪ)












