Homeዜናና ወቅታዊዜናየሕዳሴ ግድብ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ

የሕዳሴ ግድብ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተናገሩት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 11/2017 በፓርላማ እየሰጡ በሚገኙት ምላሽ እና ማብራሪያ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን በተናገሩት መድረክ፤ የበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የተለያዩ ጉዳዮች በተነሱበት መድረክ ላይ ከሕዳሴ ግደብ በተጨማሪ፤  ስለባሕር በር እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባት ዕቅድ ይፋ ተደርጓል፡፡

የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በቀጣይ ስድስት ወራት ሥራው ተጠናቆ “ሪቫን እንቆርጣለን” ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትክክለኛ ጊዜው በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ ሕዳሴ “አፍሪካዊያን በራሳቸው መሥራት እንደሚችሉ ያሳዩበት ነው” ብለዋል፡፡

አክለውም ሕዳሴ ግድብን ለመጨረስ “በርካታ ችግሮች ታልፈዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጭምር ፋይዳው የጎላ ነው፤ ግድቡ በመሞላቱ ምክንያት አስዋን ግድብ ላይ የጎደለ ውሃ የለም፤ እኛም ቃል የገባነው ይህ እንዲፈጸም ነበር” ብለዋል፡፡ “የአፍሪካ ኩራት ነው” ያሉት ግድብ፤ “ኢትዮጵያ መቻልን ያሳየችበት፤ ስሕተታችንን ያረምንበት ጭምር” ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ውሎ ካነሷቸው መካከል ሌላኛው የወደብ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም የቀይ ባሕርን በመጥቀስ፣ “ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው፤ [ ] ስለ ባሕር በር ጉዳይ ማንሳት ከእንዲህ ነውር መሆኑም ቀርቷል” ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘው “130 ሚሊዮን መለወጥ የሚፈልግ ሕዝብ፤ ጫፍ ጫፉ ተሰምሮለት ተዘግቶ እስር ቤት ሊቀመጥ አይችልም” ያሉ ሲሆን፣ “ማንም ሰላም ወዳድ ነኝ የሚል የዓለም መንግሥት፣ ግለሰብ አልያም ቡድን ከወንድሞቻችን ጋር አነጋግሮን በሕግ አግባብ እና በ‘ቢዝነስ ተርም’ አነጋግሮን እንዲያግባባን እንፈልጋለን” ሲሉ የድርድር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ የፓርላማ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ውጥን መያዙንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡ “አሁን የሕዳሴ ጉዳይ እንደምታውቁት ስለሆነ፤ የሕዳሴ ፊታችንን ወደ ማዳበሪያ እናዞራለን” ሲሉ ቀጣይ እቅድ ላይ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ ‘’በርትተን ከሠራን ቢያንስ ከሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ጊዜ ይፈልጋል’’ ብለዋል፡፡

ይህም “ሁለተኛ ህዳሴ የሚሆነው የማዳበሪያ ፋብሪካው ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ “ግንባታውን ከተቻለ ከግሉ ሴክተር ጋር በመተባበር ወይም በግል ኢንቨስትመንት ካልሆነም በመንግሥት የግድ የማዳበሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሊመልስ በሚችል መልኩ መገንባት ይኖርበታል ምናልባትም የሚቀጥለው ዓመት ሁነኛ ተግባሩ ይጀምራል’’ ብለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular