Homeዜናና ወቅታዊዜናበሕዳሴ ግድብ ምርቃት እንዲሳተፉ ለግብፅ እና ሱዳን ግብዣ ቀረበ

በሕዳሴ ግድብ ምርቃት እንዲሳተፉ ለግብፅ እና ሱዳን ግብዣ ቀረበ

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በሚኖረው የምርቃት ሥነ ሥርዐት ላይ ግብጽ እና ሱዳን እንዲሳተፉ ግብዣ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ “ክረምቱ ሲያልቅ” እንደሚመረቅ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ግብዣ ያቀረቡት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 26/2017 እየተካሄደ በሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ “ሕዳሴ ግድብ አልቋል” ሲሉ በይፋ የተናገሩት ዐቢይ፤  “ከመመረቁ በፊት ብንረብሽ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፤ ግን እናስመረቀዋለን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡  

በዚሁ ንግግር ላይ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ግድቡ ለግብፅና ለሱዳን በረከት መሆኑን በመግለጽ፤ የሚመጣው ልማትና ኢነርጂ ለሁሉም ሀገራት የሚተርፍ ከመሆኑ ባሻገር የግብጹን አስዋን ግድብ “አንድ ሊትር ውሃ አለመቀነሱን”ም አስረድተዋል፡፡  

አያይዘውም ኢትዮጵያ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ጋር “ለመነጋገር፤ ለመደራደርና ለመሥራት” አሁንም ዝግጁ መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

ክረምቱ ሲያልቅ እንደሚመረቅ የተገለጸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ ወረዳ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የግንባታው መሠረተ ድንጋይ የተጣለው መጋቢት 24/2003 ነበር፡፡ የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው። ግድቡ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ መጠን የሚይዝ ነው፡፡ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ሥፋት ደግሞ 1 ሺሕ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሆኑን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡  

በሌላ በኩል በዛሬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፤ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል፡፡ የፋብሪካውን ግንባታ መጀመሪያ ጊዜ ይፋ ባያደርጉም ተጠናቆ ሥራ የሚጀምረው “ከ40 ወራት በኋላ” እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

በዛሬው የምክር ቤት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የጋዝ ምርት ይገኝበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዝ ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ አውጥተው ወደ ተጨባጭ ስራ አይገቡም ነበር ሲሉ የተናገሩ ዐቢይ፤ኢትዮጵያ የጋዝ ምርት በቅርቡ ለገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር ገልጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular