የፍልስጤሙ ሐማስ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተዘጋጀው የጋዛ ተኩስ አቁም ምክረ ሐሳብ፤ ነገ ጁመዓ ምላሽ ሊያቀርብ መሆኑን አሸርቅ አል አውሰጥ ለጉዳይ ቅርበት ካላቸው ምንጭ ሰምቻለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡
በዘገባው መሠረት፣ የቀረበው ምክረ ሐሳብ፤ ሐማስ እና እስራኤል በድርድር ሒደት ላይ እስካሉ ድረስ ግጭቱ እንደማይቀጥል ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው፡፡ ለሐማስ የቀረበው ምክረ ሐሳብ ከዚህ ቀደም ለቡድኑ እንዲደርስ የተደረገው በዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ አማካኝነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ መቅረቡ የተገለጸው ምክረ ሐሳብ፤ እምብዛም ለውጥ የተደረገበት አለመሆኑን ዜና ምንጩ ጠቁሟል፡፡
ሐማስ ምክረ ሐሳቡ ከአሜሪካ ጋር ድርድሩን በሚመሩት ኳታር እና ግብጽ እንደቀረበለት ትናንት ረቡዕ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ቡድኑ ማረጋገጫው የሰጠበትን መግለጫ የሰጠው፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በጋዛ ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምታለች ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይህን በገለጹበት ጊዜ በጋዛ ያለው ሁኔታ “ከመባባሱ በፊት ሐማስ ስምምነቱን እንዲቀበል” አሳስበዋል።
ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ትራምፕ ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡ ትራምፕ ያቀረቡት የተኩስ አቁም ስምምነት ለሁለት ወራት ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ ጫናውን እያሳደሩ የሚገኙት በሚቀጥለው ሳምንት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ሊገናኙ እንደሆነ በተነገረበት ሰዓት ነው፡፡
ትራምፕ ለሁለት ወራት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ኔታንያሁን ለማግኘት ቀጠሮ ቢይዙም ሐማስ የተኩስ አቁም ሲደረግ “በዘላቂነት ጥቃቱን ለማስቆም መሆን እንደሚኖርበት” መግለጹን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሐማስን “እስከመጨረሻው ማስወገድ ካልቻልን ጥቃቱን አናቆምም” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤንያሚን ቤንታንያሁ የሐማስን መግለጫ ተከትሎ ከሐማስ መግለጫ በኋላ ይህን አቋም የሚያረጋግጥ ንግግር አድርገዋል፡፡
አክሲዮስ የተሰኘው የአሜሪካ የዜና አውታር እንደዘገበው ደግሞ፤ የእስራኤሉ ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ድርድር “በአፋጣኝ ካልተሳካ” የጦር ሠራዊታቸው በጋዛ ላይ የሚፈጽመውን ዘመቻ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሊያደርጉ እንደሚችሉ እየዛቱ ይገኛሉ፡፡

በትራምፕ ባቀረቡት የጋዛ ተኩስ አቁም፤ በሐማስ እጅ የሚገኙ 10 በሕይወት የሚገኙ እንዲሁም 18 ሙታን መካከል ግማሹ በመጀመሪያው ቀን፤ ቀሪዎች ደግሞ በተኩስ አቁሙ ሰባኛው ቀን እንዲለቀቁ የሚያደርግ ነው፡፡ በምላሹ በእስራኤል የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውን 125 ፍልስጤማውያን እስረኞች፣ እ.አ.አ ከጥቅምት 7/2023 በኋላ በጋዛ በእስራኤል ወታደሮች ተይይው በማጎሪያ ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያንም እንዲለቁ የሚጠይቅ ነው፡፡
ጉዳዩን የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት፤ ፍልስጤማውያን በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያላቸው እምነት በመሸርሸሩ የቀረበው ምክረ ሐሳብ ተግባራዊነት ላይ ጥርጣሬ ስለገባቸው እምብዛም ተስፋ አልጣሉበትም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












