
የ ካሊድ መንገድ
ከካሊድ ጋር የተዋወቅነው ትምህርት ቤት ነው፡፡ ፈታ ያለ ልጅ ነው፡፡ ምንም ነገር ለማድረግ ከቤተሰቡም ሆነ ከሌሎች ሰዎች አይደባበቅም፡፡ ይቅማል፣ ያጨሳል- ማለቴ ሺሻም ይሞክራል፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔና ሌሎች በቡድን የምናስብና የምንንቀሳቀስ የካሊድ ጓደኞች ጫትም ሆነ ሺሻ የለመድነው እሱን ታከን ነው ብል ለእውነት ሩብ ጉዳይ ሀቅ እንዳወራሁ ነው የሚሰማኝ፡፡
ምላሱ ላይ የተነቃሳት የምትመስለን የካሊድ እናት የሁላችንም እናት እንደዛ በሆኑልን ብለን እስክንመኝ ትመቸናለች፡፡ ባጠቃላይ የካሊድ አኗኗር ህልማችን ነው፡፡ እርግጥ ነው ከሱ ጋር በነበረን ትስስር ከዲናችን እየራቅን መምጣታችን ሳይታወቀን ነጉደን ነበር፡፡ እስማኤል እስኪቀላቀለን፡፡ ባጭሩ እስማኤል ሙሴያችን ሆኖ ታደገንና የተበላሸው ሂወታችን መስመር እየያዘ ወደ አላህ እየተቃረብን በኢባዳ እየበረታን‹ ከሱስ እየተፋታን መጣን፡፡
የዚህን ጊዜ በካሊድና በእናቱ መሃከል ያለው ክፍተት በደንብ ገባን፡፡ ካሊድ በዙርያው ጓደኛ እንጂ ቤተሰብ እንደሌለው ተረዳን፡፡ እንዴት ማለት ጥሩ… እንዴት በሉ… የካሊድ እናት ካሊድን ስትወልድ ልጅ ወልዶ ለማሰደግም ሆነ ከስሜት ከፍ ብሎ ስለማሰብ ደንታ አልነበራትም፡፡
ይህን ስል አዝናለሁ ነገር ግን የሆነው እንደዛ ነው… አለማወቅ ሊሆንምኮ ይችላል፡፡ ቢሆንም ካሊድ ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገው ፐ! ዘመናዊ እናትስ እንደሱ እየተባለ በሌሎች እየተቀናበት ቢሆንም… በዘመናዊነት ስር የተደበቀው የናቱን የናትነት ሚና መጉደል ማንም ሳያስተውልለት ክፍተቱን እያሰፋ ነው ያደገው፡፡ እናቱ ከልጇ ፊት ልትደብቀው ያልቻለችው አላህን የሚያስቆጣ ባህሪና ተግባራቶቿ በሱ የልጅነት ሚዛን ልክ ናቸው ተብለው ሲሰፈሩ ነው ያደገው፡፡
ወላጆቹ ጥፋታቸውን፣ የወላጅነት ሚናቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት የሚመጣውን ቀውስ ለልጃቸው የፈለገውን ነገር እንዲያደርግ በመፍቀድ ነው ያካካሱት፡፡ በህይወቱ ክልከላ የለም፡፡ ህግ የለም፡፡ ስርዓት የለም፡፡ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደሚችል ነው የሚያውቀው፡፡ መቃም የፈለገ ቀን እናቱ ጋር ፈርሾ፣ መውጣት የፈለገ ቀን ሴት ጓደኞቹን በናቱ ስልክ ጠርቶ ማማዬ ዛሬ አድራለሁ አትጠብቂኝ ብሎ ራስህን ጠብቅ ተብሎ ነው የኖረው፡፡ ከሙስሊም ቤተሰብ ቢወለድም የእስልምና ድንበር የት ድረስ እንደሆነ ሳይነገረው፣ ከዚህች ሀገር ተሸግሮ ሌላ ህይወት እንደሚጠብቀው ሳያውቅ ነው የኖረው፡፡
ከኛ ጋር የገጠመ ሰሞን ለሰላት የምናሳየው መጠዳደፍ ይገርመው ነበር፡፡ በዚህ እድሜያችን ለመስገድ ማሰባችን ራሱ ይደንቀዋል፡፡ ለሱ የሚገባው ሰላት የትልልቅ ሰዎች ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ ዲን ማለት ለሱ ቤታቸው ተፈርሾ ዱኣ ሲደረግ አሚን፣ አሚን በሚባለው ኢባዳ የተወሰነ ነው፡፡ ሙስሊም መሆኑን ቢያውቅም እስልምና እንደብሄሩ ወይም ጾታው የተጫነበት አንድ ማንነት እንጂ ህግና ስርዓት ያለው የህይወት መመርያ መሆኑን አያውቅም፡፡
ቁርዓን መቅራት ቢችልም ወደ አላህ በመከጀል ሚቃረቡበት መሳርያ መሆኑን አይገነዘብም፡፡ ባጠቃላይ ለሱ አለም እናቱ ባሰመረችለት መስመር ውስጥ የሚርመሰመስ ዑደት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡